የሀገራችን ልሂቃን በጥቅሉ “የብሔርተኝነት እና የአንድነት አቀንቃኞች” በሚል ለሁለት መክፈል ይቻላል። አብዛኛውን ግዜ በሁለቱ ወገኖች መካከል መጯጯህ እንጂ መደማመጥ የለም። በመካከላቸው በመግባባት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ አይቻልም። በእርግጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ምሁራን የገላጋይነት ሚና ይጫወታሉ። ሆኖም ግን፣ ምሁራንም የእብድ ገላጋይ ከመሆን አላለፉም።
የፖለቲካ ልሂቃኑ በጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየት ከተሳናቸው ብሔራዊ መግባባት (national consensus) ሊኖር አይችልም። ብሔራዊ መግባባት በሌለበት በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ግራ-መጋባት እና አለመተማመን ይሰፍናል። የብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) በግራ-መጋባትና አለመተማመን ውስጥ ሲወድቅ ለጨቆና ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
በመሠረቱ የመንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚወሰነው በብዙሃኑ አመለካከት ነው። ምክንያቱም፣ አምባገነን ሆነ ጨቋኝ መንግስት በብዙሃኑ አመለካከት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር አይፈፅምም። አንድን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ባይደግፍ እንኳን በጋራ የማይቃወም መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። እንዲህ ያለ ማህብረሰብ የሚፈጠረው ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃኑ እርስ-በእርስ መግባባት ሲሳናቸው ነው። የልሂቃኑ አለመግባባት በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ግራ-መጋባትና አለመተማመን እንዲሰፍን ያደርገዋል። ግራ-የተጋባና እርስ-በእርሱ የማይተማመን ሕብረተሰብ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት የለውም። በመሆኑም፣ የመንግስትን ተግባር ባይደግፍ እንኳን በጋራ አይቃወምም።
ከላይ በተጠቀሰው መሠረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት ፍፁም አምባገነናዊና ጨቋኝ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ለምሳሌ፣ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ ባይደግፍም በጋራ አይቃወምም። ስለዚህ፣ ከጨቋኝ ስርዓት በፊት እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት የተሳናቸው ልሂቃን፣ በዚህ ደግሞ ግራ-የተጋባና የማይተማመን ሕብረተሰብ መፈጠር አለበት።
የኢህአዴግ መንግስት የተፈጠረው በዚህ አግባብ ነው። በእርግጥ አሁን ያለው የብሔር የፖለቲካ በራሱ በ1960ዎቹ የነበረው የብሔርተኝነት እና አንድነት ፖለቲካ ውጤት ነው። በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ግን የብሔርተኝነት ሆነ የአንድነት አራማጅ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ፍፁም አምባገነናዊ ነው። መነሻው ብሔርተኛ ይሁን እንጂ ከብሔርተኞች ጋር ስምምነት የለውም። ከእሱ የተለየ ሃሳብ ያነሱ ብሔርተኞችን በጠባብነት፣ የአንድነት አቀንቃኞችን ደግሞ በትምክህተኝነት ይፈርጃል። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ ሲሄዱና ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲፈጥሩ ደግሞ በሽብርተኝነት ወንጀል ይከሳቸዋል።
በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት ጨቋኝና አምባገነን እንዲሆን ያስቻሉት የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው። ልሂቃኑ እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት ስለተሳናቸው ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል ግራ-ተጋብቷል፣ መንግስት ደግሞ ይበልጥ አምባገነን ሆኗል። ስለዚህ፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካ መሰረታዊ ጥያቄ “የፖለቲካ ልሂቃኑ ለምን እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት ተሳናቸው?” የሚለው ነው። የዚህ ደግሞ መልሱ አጭርና ግልፅ ነው፡፡ አዎ…እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙሃኑ የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን “የትላንት ምርኮኞች” ናቸው። “ለምንና እንዴት” የሚለው በቀጣይ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን። ለአሁኑ የትላንት ምርከኞችን አመለካከት በአጭሩ በመዳሰስ ፅሁፌን ላብቃ፡፡
የትላንት ምርከኞች ጨዋታ ስለወደፊቱ ሳይሆን ስላለፈው ነው። ነገር ግን፣ ትላንት የሄደ፥ ያለፈ ነገር ስለሆነ አይቀየርም። የከርሞ ሰዎች ደግሞ ስለ ነገ ይወያያሉ። ነገ ተስፋ ነው። የነገ ተስፋ ይቀየራል፤ ብሩህ ወይም ጭለማ ይሆናል። የትላንት ምርኮኞች ስለ ትላንቱ በደል እና ድል ያወራሉ። ስለ ትላንቱ በደል ብቻ ማውራት ቂምና በቀል ይወልዳል። ስለ ትላንቱ ድል ብቻ ማውራት ባዶ ጉራ፥ የማቃት ስቅታ ይሆናል። የከርሞ ሰው ከትላንቱ በደልና ድል ይልቅ ስለ ነገ ተስፋና እድል በጋራ ይወያያል። የትላንት ምርኮኞች ስላለፈው የተናጠል በደልና ድል ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ይጯጯሉ፥ ይጠላለፋሉ።
No comments: