Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

ብቻህን አይደለህም - ዳንኤል ክብረት



ብቻህን አይደለህም - ዳንኤል ክብረት

የቼሮቄ ጎሳዎች በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ የነበሩ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የቼሮቄ ወጣቶች ለዐቅመ አዳም መድረሳቸውን የሚገልጡበት አንድ ከባድ ፈተና አላቸው፡፡ ወጣቱን አባቱ ይዞት ሊመሻሽ ሲል ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ ዓይኑን በጨርቅ ይታሠራል፡፡ ምንም ነገር ለማየት አይችልም፡፡  

ያንን ጨርቅም ከዓይኑ ላይ ለማንሣት አይፈቀድለትም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ይቀመጣል፡፡ ከተቀመጠበት ቦታም መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም፡፡ ጨለማው አልፎ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ በዚያ ጫካ ውስጥ ለብቻው አንድ ቦታ ተቀምጦ ማሳለፍና ‹ወንድነቱን› መፈተን አለበት፡፡ አካባቢው ጸጥ ያለ ነው፡፡ 

ከአራዊት ጩኸትና ኮሽታ በቀር ሌላ የለበትም፡፡ ሰውም በአካባቢው አይደርስም፡፡ ምግብና ውኃ የሚያቀብለውም የለም፡፡ የልብ ምቱን እያዳመጠ ሌሊቱን በጸጥታ ያሳልፈዋል፡፡ ይህን ሌሊት ያለ ችግር ለማሳለፍ የቻለ ወጣት ለዐቅመ አዳም ደረሰ ማለት ነው፡፡ እንዴት እንዳሳለፈውና ምን እንዳጋጠመው ከእርሱ በታች ላሉት ልጆች ለመናገር አይፈቀድለትም፡፡ እያንዳንዱ ወንድ የራሱን ማንነት በባህሉ መሠረት መፈተሽ አለበትና፡፡ 

በዚህ ሥርዓት መሠረት አንድ የቼሮቄ ወጣት በምሥራቅ ቴነሲና በሰሜን ካሮላይና ወደሚገኘው የቼሮቄ ደን ተወሰደ፡፡ ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን እያየ ነው የተጓዘው፡፡ አባቱ የዓይን ማሠሪያውን ጨርቅ ይዟል፡፡ ሌሎች ሸኚ የጎሳ አባላት ደግሞ ይከተሉታል፡፡ ጥቅጥቅ ያለውን ደን አቋርጠው ከዛፎቹ ርዝማኔ የተነሣ ፀሐይን ለማየት ወደማይቻልበት ሆድ ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሊቱን የማሳለፊያው ቦታ ተመረጠ፡፡ ወጣቱም ዓይኑን በጨርቅ ታሠረ፡፡  


ታዛቢዎችም ዓይኑ በሚገባ የታሠረ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ከዚያም አንድ ቦታ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ሰዎች ተራ በተራ እየተሰናበቱት አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ፡፡ ኮቴያቸው እየራቀው እየራቀው ሲሄድ ይታወቀዋል፡፡

አካባቢው ጸጥ ረጭ አለ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የዛፎቹ ንጽውትውታ ይሰማ ነበር፡፡ ነፋሱና ቅጠሎቹ ኅብረት ፈጥረው እያዝናኑት ነበር፡፡ እየቆየ ግን ሁሉም ነገር ረጋ፡፡ እዚህም እዚያም ‹ኮሽ› የሚል ነገር ይሰማል፡፡ ቱርር ብለው የሚያልፉ ነገሮች አሉ፡፡ በቼሮቄ ተረቶች ውስጥ ስለ ቼሮቄ ደን የሰማቸውን ተረቶችና ታሪኮች አስታወሰ፡፡ 


አዳኞች ወደዚህ ጫካ መጥተው ያፈጸሟቸው ጀብዱዎች፣ ያጋጠሟቸውንም ፈተናዎች፣ ያለፉባቸውንም ውጣ ውረዶች ይተርኩ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ደኑን በእግር አቋርጦ መውጣት ራሱ እንደ ጀግንነት ይቆጠር ነበር፡፡ መጀመሪያ በበትር እየገለጡ ለመሄድ የሚስቻለው ደን እየቆየ ግን ዓይን እስከመውጋት ይደርሳል፡፡ 

ጥቅጥቅ ይልና ቀኑን ጨለማ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ደን ውስጥ አልፎ አልፎ በጎሳዎች መካከል ውጊያ እንደተደረገ ይወራል፡፡ሌሊቱ እየጨመረ ሲሄድ ፍርሃት ይመጣበት ጀመር፡፡ ለምን እዚህ እንደመጣ፣ ይህንን ፈተና ሲያልፍ የሚያገኘውን ክብር፣ ክብሩ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡና ለጎሳው ሁሉ እንደሚተርፍ ሲያስበው እንደገና የብርታት መንፈስ ይወረዋል፡፡ 

650ሺ ሄክታር በሚደርሰው የቼሮቄ ደን ውስጥ ከ20 ሺ በላይ የእንስሳትና የዕጽዋት ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ ረዣዥም ተራሮች፣ ጫካ አቋርጠው የሚጓዙ ወንዞች፣ ገበታ የመሰሉ ሸለቆዎች፣ አስቸጋሪ ገደላ ገደሎችና ለጥ ያሉ ሜዳዎች በውስጡ አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ወጣቱ ያስባቸዋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀውና የሚያስፈራው አንድ ነገር ነው፡፡ ብቻውን መሆኑ፡፡ ቼሮቄዎች ‹አሲ› ብለው በሚጠሯቸው ባህላዊ ቤቶቻቸው ውስጥ በአንድ ቤት አብረው የሚያድሩት ብዙ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ብቻውን የሚኖርም ሆነ ብቻውን የሚያድር የለም፡፡ አደን ሲሄዱ በጋራ ነው፤ ወንዝ ሲወርዱም በጋራ ነው፡፡ 


አሁን ግን ለብቻው በቼሮቄ ደን ውስጥ ያውም በሌሊት ቁጭ ብሏል፡፡ ዕንቅልፉ ይመጣና ይሄዳል፡፡ ብርታቱ ይመጣና በፍርሃት ይተካል፤ እንደገና ደግሞ በጀግንነት ስሜት ይወረራል፡፡ አንዳች አውሬ ቢመጣበት ምን ለማድረግ ይችላል? ሳያየው በድምጹና በአካሄዱ ብቻ ማንነቱን መለየት አለበት፡፡ 

ዓይኑ እንደተሸፈነ መከላከልና መቋቋምም አለበት፡፡ ያውም ብቻውን፡፡ የሚረዳው የለም፤ ምን እንደሆነ እንኳን ታሪኩን ሊነግርለት የሚችል የለም፡፡ቢቆስል የሚያያክመው፤ አውሬው ይዞት ቢሄድ የሚያስጥለው የለም፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያስብ ፍርሃቱ ያይላል፡፡

በሐሳብ ወዲያና ወዲህ እየተማታ ሌሊቱ ይገሠግሣል፡፡ አራዊቱ ይጮኻሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በአጠገቡ ናቸው፡፡ ከሹክሹክታ፣ እስከ ግሣት፣ ከሲርታ እስከ ፉጨት ድምጻቸው ይመጣል ይሄዳል፡፡ ዙሪያውን እየከበቡ የሚተራመሱ አራዊትም አሉ፡፡ በእግሩ ሥር ሲያልፉ፤ ሰውነቱን ታክከውት ሲሄዱ ይሰማዋል፡፡ ባህሉ ግን ካለበት ቦታ እንዲነቃነቅ አይፈቅድለትም፡፡ በጽናትና በትዕግሥት፣ ያለ ፍርሃትና ያለ ጭንቀት ባለበት እንደተቀመጠ የፀሐይዋን ምጽአት መጠበቅ አለበት፡፡ 


አራዊቱም፣ ነፍሳቱም፣ የጫካው ግርማም አያስጨንቀውም፡፡ የሚያስጨንቀው በዚያ ከልጅ እስከ ቅመ አያት በአንድነት በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ አድጎ በዚህ ጫካ ውስጥ ብቻውን መሆኑ ነው፡፡ ከአራዊቱ ይልቅ ብቸኝነቱ ያስፈራዋል፡፡ ለአራዊቱ አራዊት፣ ለነፍሳቱም ነፍሳት፣ ለዛፎቹም ዛፍ አላቸው፡፡ እርሱ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ተመኝቶ አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ናፍቆት አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡  


ሌሊቱ እየገሠገሠ ነው፡፡ ድካሙም እየጨመረ ነው፡፡ በዚያ የብርታቱ ሰዓት ያልመጡት አራዊት በዚህ የድካሙ ሰዓት ቢመጡ ምን ሊውጠው ነው? የኦኮናሉፍቴ ወንዝ ከዐለቱ ጋር እየተጋጨ ሲወርድ የሚፈጥረው ድምጽ ይሰማዋል፡፡ ወንዙ ከዐለቱ ጋር የሚጋጭበት ጋ ሲደርስ መልኩ ቡናማ ይሆናል፡፡ ወዲያው ደግሞ አካባቢው ቀስተ ደመና ይፈጥራል፡፡ አሁን ግን ሌሊት ነው፡፡ ምን እየሆነ እንደሆን አያውቅም፡፡ 


ሸለብ ሊያደርገው ሲሞክር የወፎቹን ድምጽ ሰማ፡፡ እየነጋ መሆኑን ሲያስብ ብርታቱ ተሰብስቦ መጣ፡፡ የመከራው ሌሊት እያለፈ ነው፡፡ ለዐቅመ አዳም የሚደርስበትና ሠፈሩ በከበሮ የሚናወጥበት ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ ጥቂት ከቆየ ፀሐይዋ ብቅ ትላለች፡፡ ዓይኑ የተሸፈነበትን ጨርቅ ማሞቅ ስትጀምር ያን ጊዜ ጨርቁን ይፈታዋል፡፡ ይህንን የብቸኝነት ጫካ እየዘለለ ለቅቆ ጎሳው በጉጉት ወደሚጠብቅበት ሥፍራ ይገሠግሣል፡፡  


እንደጠበቃት ፀሐይዋ መውጣቷን ዐወጀች፡፡ ዓይኑ የታሠረበት ጨርቅ መሞቅ ጀመረ፡፡ አሁን ጨርቁን መፍታት ይችላል፡፡ ብርዱ ያቆረፈደውን እጁን አፍታትቶ ጨርቁን በፍጥነት መፍታት ጀመረ፡፡ ቋጠሮዎቹን ቀስ በቀስ አላቅቆ ዓይኑን ነጻ ሲያወጣ፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች አካባቢው ተደናበረበት፡፡ 


ጸጥ ብሎ ቆየና ዓይኖቹን አሻቸው፡፡ ቀስ በቀስም አካባቢው በብርሃን እየተገለጠለት መጣ፡፡ ፊት ለፊት ወዳለው ጫካ ዓይኑን ሲወረውር ጉብታው ላይ አባቱን አየው፡፡ ውርጩ በላዩ ላይ ዘንቦበታል፡፡ ጦሩን ተክሎ ቀስቱን አንግቶ ተቀምጧል፡፡ 

ተወርውሮ ሄደና አቀፈው፡፡ ‹መቼ መጣህ?› አለው የልብሱ ቅዝቃዜ እየተሰማው፡፡

‹እዚሁ ነበርኩ› አለው አባቱ፡፡
‹ከመቼ ጀምሮ› አለው ልጁ፡፡
‹ከመጀመሪያ ጀምሬ›
‹ሌሊቱን እዚህ ነው እንዴ ያደርከው›
‹አዎ›
‹እኔኮ ብቻየን የሆንኩ መስሎኝ ነበር›
‹ብቻህን አልነበርክም፡፡ እኔ በንቃት እየተከታተልኩህም፣ እየጠበቅኩህም ነበር፡፡ አንተ ስታሸልብ እኔ ግን አላሸልብም ነበር፡፡ እዚሁ ነበርኩ፡፡ እያየሁህ ነበር፡፡ ምናልባት ግን ስለማታየኝ የሌለሁና ብቻህን የሆንክ መስሎህ ይሆናል፡፡ ግን አልነበርክም፡፡ ይህችን ቅጠል ታውቃታለህ? › አለው አባቱ ጎንበስ ብሎ አንዲት ሸካራ ቅጠል እየቆረጠ፡፡
‹አላውቃትም› አለ ልጁ፡፡
‹ይህቺ ቅጠል እባብና እርሱን የመሰሉትን የምታባርር ናት፡፡ ሽታዋን ከሩቁ ካሸተቱ በአካባቢዋ አይቀርቡም› አለው፡፡ 

ያንን ወንዝስ ታውቀዋለህ?› አለው በሩቁ ፀሐይዋ የምትንቦጫረቅበትን ወንዝ እያሳየ፡፡ 

‹እርሱንማ አውቀዋለሁ፤ የኦኮናሉፍቴ ወንዝ አይደል እንዴ› አለና መለሰለት፡፡ ‹ታድያ የቱ አውሬ ነው ይህንን ገደላማ ወንዝ ተሻግሮ የሚመጣብህ› አለ አባቱ እየሳቀ፡፡ ልጁም ሳቀ፡፡ ‹ይህንን ሌሊት ሌሊት የሚመጣ ወፍስ ታውቀዋለህ› አለና አንድ ሽው ብሎ ያለፈ ወፍ አሳየው፡፡ ልጁ ወፉን ለማየት የሚችልበት ርቀት ላይ አልነበረም፡፡ ወፉም በሽውታ ነው ያለፈው፡፡ 

‹አላየሁትም› አለው ልጁ፡፡


‹ይህ ወፍ ሌሊት ሌሊት ያጉረመርማል፡፡ እርሱ ወደሚያጉረመርምበት ቦታ አራዊት አይቀርቡም፡፡ እነዚህ ሁሉ ሳያውቁህና ሳታውቃቸው አንተን ሲጠብቁህ ነው ያደሩት፡፡ አየህ ልጄ አብረውህ ሲጠብቁህ ያደሩ ብዙ ናቸው፡፡ ወንዙ፣ ዛፉ፣ ተራራው፣ እነዚህ ሁሉ አብረውህ ነበሩ፡፡ 


ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ አባትህ አብሬህ ነበርኩ፡፡ አንተ ግን ብቻዬን ነበርኩ አልክ፡፡ ብቸኝነትህን ያመጣው ብቻህን መሆንህ አይደለም፡፡ አብሮህ ያለውን አለማወቅህ እንጂ፡፡ ከዚህ ሌሊት እንድትማር የምንፈልገው አንዱ ትምህርት ሰው ምንጊዜም ብቻውን እንዳልሆነ እንድታውቅ ነው፡፡ 

አካባቢህን ካላወቅህ በሰዎች መካከል ሆነህ እንኳን ብቻህን ትሆናለህ፡፡ አካባቢህን ካወቅከው ግን መቼም ብቻህን አትሆንም፡፡› 

አባትና ልጅ በደስታ እየተጨዋወቱ ከጫካው ወጥተው በጉጉት ወደሚጠብቃቸው ሕዝብ ተቀላቀሉ፡፡

ኩሬአውያን - ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ኩሬአውያን - ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ትውፊታውያን የሀገራችን ሰዓሊዎች የማያመዛዝንን ሰው ሲስሉ አንድ ዓይና አድርገው ይስሉት ነበር፡፡ ሰፋ አድርጎ የማያይ፤ እውነትን በከፊል ብቻ የሚቀበላት፤ ከሚያውቀው ውጭ ሌላ ነገር ያለ የማይመስለው ነው ማለታቸው ነው፡፡ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› የሚል አባባልም አለ፡፡  

ዕውቀትህን፣ አመለካከትህንና አካሄድህን ባሻሻልክ ቁጥር ያላየኸውን ታያለህ፣ ያልሰማኸውን ትሰማለህ፤ ያልተገለጠልህ ይገለጥልሃል፤ የረቀቀው ይጨበጥልሃል፤ እውነት ነው ያልከው ውሸት፣ ውሸት ነው ያልከውም እውነት ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ ሲሉ ነው፡፡ 

ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችን በሌላው የሌላውን ለማየት ነው፡፡ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ ለመስጠት በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ ወደራሳችን በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡
ሞንጎልያውያንም ከዚህ ጋር የሚሄድ ብሂል አላቸው፡፡  

በአንዲት የሞንጎልያ ትንሽ መንደር ውስጥ በምትገኝ ኩሬ አንዲት ዓይን ብቻ ያለቺው ዕንቁራሪት ይኖር ነበር፡፡ ለእርሱ ዓለም ማለት ያቺ ኩሬ፣ ንጉሥም ማለት እርሱ ነው፡፡ ከእርሱ ኩሬ የተሻለ ቦታ፣ ከእርሱም የበለጠ ዕድለኛ የለም፡፡ የሚመኘው ነገር ቢኖር እርሱ ያገኘውን ይህንን ታላቅ ነገር የሚካፈለው ጓደኛ እንዲያገኝ ብቻ ነበር፡፡  

አንድ ቀን በአካባቢው ከባድ ዝናም ጣለ፡፡ ምድሪቱንም የሚገለባብጣት መሰለ፡፡ ዕንቁራሪቱ በዚያች ለእርሱ ምርጥ በሆነችው ኩሬ ውስጥ በመሆኑ ምንም ነገር አይመጣብኝም ብሎ አመነ፡፡ ዝናቡ ግን አካባቢውን ደበላልቆ ከኩሬው ማዶ የሚገኘውንና ዕንቁራሪቱ መኖሩን የማያውቀውን ኡቩስ ኑር የተባለውን ጨዋማ ባሕር እንዲሞላ አደረገው፡፡

ባሕሩ ሲሞላ በውስጡ የነበሩትን እንስሳት ተፋቸው፡፡ አንዱ የባሕር ዔሊም በጎርፉ ተወስዶ የማያውቀው ቦታ ወደቀ፡፡ ዔሊው የኡቩስ ኑር ባሕርን ሊያየው አልቻለም፡፡ የት ቦታ እንዳለም አላወቀም፡፡ 

ወደየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበትም ግራ ገባው፡፡ ነገር ግን በቆሙበት ቦታ ከመሞት እየሄዱ መሞት ይሻላል ብሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ ቢሄድ፣ ቢሄድ፣ ቢሄድ መንገዱ ሊያልቅለት ባሕሩንም ሊያገኘው አልቻለም፡፡እንዲያውም እየደከመውና እየራበው መጣ፡፡ ሙቀቱንም መቋቋም አልቻለም፡፡ ወደ ኡቩስ ኑር ባሕር ሳልደርስ ልሞት እችላለሁ ብሎ ሠጋ፡፡  

ወደ ባሕሩ በቀላሉ ሊደርስ እንደማይችል የተረዳው ዔሊ ነፍሱን ሊያድንለት የሚችል አንዳች ውኃ እየፈለገ ሳለ የዕንቁራሪቱን ኩሬ ተመለከተ፡፡ በዔሊ ፍጥነት ተንከላውሶ እዚያ ኩሬ ውስጥ ተወርውሮ ዘፍ አለ፡፡ ዔሊው ኩሬው ውስጥ ዘፍ ሲል የኩሬው ውኃ ከጥፋት ውኃ ባልተናነሰ ተናወጠ፡፡ 

ዕንቁራሪቱም ሰምቶት የማያውቀውን በመስማቱና አይቶት የማያውቀውን በማየቱ በድንጋጤ ልቡ ቀጥ አለች፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሲረጋጋ አንዳች የሚያህል ፍጡር በኩሬው ውስጥ ሲንከላወስ ተመለከተ፡፡  

‹ለመሆኑ ማነህ? ከየትስ መጣህ? እዚህስ ምን ታደርጋለህ?› የጥያቄ መዓት አወረደበት፡፡ ዔሊው ጥሙን የሚያስታግሥለትን ውኃ ከተጋተ በኋላ ‹እኔ ዔሊ ነኝ፡፡ የመጣሁትም ከኡቩስ ኑር ባሕር ነው፡፡ እዚያ በተከሠተ ጎርፍ ከባሕሩ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ወደ ባሕሩ እመለሳለሁ ብዬ ስጓዝ በውኃ ጥም ልሞት ደረስኩ፡፡ ፈጣሪ ይመስገን እዚህ ኩሬ ውስጥ ጣለኝ› አለው፡፡  

‹ታድያ አሁን ምን እያሰብክ ነው?› አለው ዕንቁራሪቱ፡፡ ‹እኔ ወደ ባሕሩ መመለስ ነበር የምፈልገው፡፡ ነገር ግን መንገዱን አላውቀውም፡፡ በመካከልም በውኃ ጥም እንዳልሞት ፈራሁ፡፡ እናም ካላስቸገርኩህ በጋው እስኪያልፍ እዚህ አንተ ጋ ብከርም ምን ይመስልሃል?› አለው፡፡ ለብዙ ዘመናት ብቻውን የኖረው ዕንቁራሪት ጓደኛ ስላገኘ ደስ ብሎት ፈነጠዘ፡፡ ይህን እርሱ በኩሬው ውስጥ ያገኘውን ልዩ ደስታና ርካታ የሚያካፍለው ጓደኛ አገኘ፡፡

ዔሊው የበጋውን ወቅት የሚያሳልፍበት ቦታ በማግኘቱ እፎይ ያለ ቢመስለውም ዕንቁራሪቱ ግን በጥያቄዎች ያጣድፈው ነበር፡፡ ከኩሬው ውጭ ያለውን ዓለም የማያውቀው፤ በዓለም የመጨረሻው፣ ትልቁና ምቹው ቦታ ኩሬው የሚመስለው ዕንቁራሪት የጥያቄ ናዳ አወረደበት፡፡ ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር እንደዚህ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡  

ዔሊውም ዕንቁራሪቱን ላለማስከፋት ብሎ ‹ያንተ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዕንቁራሪቱም በዚህ ተደሰተና ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር ከእኔ ኩሬ ይበልጣል› አለው፡፡ ዔሊውም ‹የኡቩስ ኑርን ባሕር ከዚህ ትንሽ ኩሬ ጋር ማነጻጻር የማይታሰብ ነው፡፡ ወርድና ቁመቱን ማንም ሊለካው አይችልም፤ አጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ምቹ ነው፡፡ አያሌ የባሕር እንስሳት ይገኙበታል› አለና መለሰለት፡፡  

ዕንቁራሪቱ ደነገጠ፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የገባው እጅግ ውሸታም ዔሊ ነው ብሎ አመነ፡፡ ከዚህ ኩሬ የበለጠ ነገር በዓለም ላይ ሊገኝ አይችልም፡፡ ዕንቁራሪቱ በአንድ ዓይኑ ሲያያት የእርሱ ኩሬ ለእርሱ እጅግ ሰፊ፣ ማንም ሊደርስባት የማይቻላት ናት፡፡ 

ለመሆኑ በዓለም ላይ ከዚህ የሚበልጥ ምን ምቹ ቦታ ይገኛል? ብሎ አሰበና ‹የኡቩስ ኑር ባሕር የሚባል ነገር የለም፡፤ ቢኖርም ከዚህ ኩሬ ፈጽሞ ሊበልጥ አይችልም፡፡ አንተ ውሸታም ነህ፡፡ ሆን ብለህ እኔን ለማስደነቅና ከዚህ እንድወጣ ለማድረግ ነው እንጂ ከዚህ የሚበልጥ ባሕር ፈጽሞ የለም፡፡ በዓለም ላይ ያለው ብቸኛው፣ ታላቁና ምቹው ውኃ ይሄ ኩሬ ነው› አለው፡፡  

ዔሊውም ‹ወዳጄ ሞኝ አትሁን፡፡ የማታውቀውን ነገር ሁሉ የለም አትበል፡፡ አንተ በአንድ ዓይንህ ስለምታያት ይቺ ኩሬ ትልቅ ትመስልሃለች እንጂ እንኳን ከዚህ ኩሬ ከኡቩስ ኑር ባሕር የሚበልጡም አሉ፡፡ እኔ የያዝኩት ብቻ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ዕውቀቴ የመጨረሻው ነው ብሎ እንደሚያስብ ፍጡር የሚጎዳ የለም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕንቁራሪቱ ክፉኛ ተቆጣ ‹ሞኝ አልከኝ፡፡ 

አንተ ከሌላ ዓለም የመጣህ ፍጡር ነህ፡፡ ከዚህ ኩሬ የሚበልጥና የተሻለ ነገር አለ ብሎ የሚለኝ ለእኔ የመጨረሻው ውሸታም ነው፡፡ ይህን ኩሬ እስካሁን እኔ ዋኝቼ አልጨረስኩትም› እያለ አመናጨቀው፡፡ ዔሊው ይህንን ንግግር ለማመን አልቻለም፡፡ የዕንቁራሪቱን ደኅነኛ ዓይን እያየ ‹አንተ ይህቺን ኩሬ የዓለም መጨረሻ አድርገህ ማየትህ አይገርመኝም፡፡ ያለህ አንድ ዓይን ብቻ ስለሆነ፡፡ 

የሚገርመው በሁለት ዓይኑ የሚያየውን ሁሉ መቃወምህ ነው፡፡ ሁላችንም በአንተ አንድ ዓይን ልናይ አንችልም፡፡ ላንተ ያልታየህ ሁሉ የለም፤ አንተ ያልደረስክበት ሁሉ አልተፈጠረም፤ አንተ ያልኖርክበት ሁሉ ምቹ አይደለም ብለህ ታስባለህ፡፡ ዓለምን በልክህ ቀደህ ሰፍተሃታል፡፡ ሁላችንም ደግሞ ባንተ ልክ እንድናሰፋት ታስባለህ፡፡  

ይህ የመጨረሻው ሞኝነት ነው፡፡ እኔ ብቻ እና የኔ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ማሰብ ነው ከዚህ ኩሬ እንዳትወጣ ያደረገህ፡፡ ሁሉንም ነገር በኩሬው ልክ ታስበዋለህ፡፡ በእውነትም አንተ የመጨረሻው ሞኝ ነህ፡፡
ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላውና ሌላውንም ለመስማት ትፈልግ ነበር፡፡ 

ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የሚያንስም፣ ካንተ የሚስተካከልም፣ ካንተ የሚበልጥም መኖሩን አምነህ ትቀበል ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላው ዐውቀህ ኅሊናህን ታሰፋው ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የተለየ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ታዳምጥ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለመስማት ዕድል ትሰጥ ነበር፡፡ 

በል ይመችህ፤ እዚሁ ኩሬህ ውስጥ ኑር፡፡ እውነትም ከዚህ የተሻለ ላንተ አይገኝም፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የምትኖረው ኩሬው ከሁሉም የሚበልጥ ስለሆነ ሳይሆን ላንተ ስለሚመጥንህ ነው፡፡ ቀሪ ሕይወቴን ከሞኝ ጋር ከምኖር ብልሆች ወዳሉበት እየሄድኩ ብሞት ይሻለኛል› ብሎ ከኩሬው ወጥቶ ሄደ፡፡  

ዕንቁራሪቱም በአንድ ዓይኑ ሲያይ የኩሬውን ግድግዳ ተመለከተው፡፡ ‹ይህ የዓለም ዳርቻ አይደለምን፡፡ ለመሆኑ ይህ ዔሊ ከዓለም ዳርቻ ውጭ የት ሊሄድ ነው› አለ ይባላል፡፡ 

ኪችነር፣ ካናዳ

የገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ሃሳቦች እና ግጥሞች

የበላይ በቀለ ወያ ሃሳቦች እና ግጥሞች

አንድ ሰው "አንባቢ ነኝ" ካለ ማንበቡ ፣ ማወቁ ፣ መማሩ ፣ ከክፋት ካላራቀው ፣ ከምቀኝነት ካላሸሸው፣ ሻጥረኛ አሻጥረኛ ተንኮለኛ ስስታም ፣ ሀሜተኛ ፣ ደበኛ፣ ቂመኛ ፣ ወረኛ ፣ ነገረኛ ፣ ትእቢተኛ ፣ እብሪተኛ ፣ ራስን ቆላይ፣ አስመሳይ!!! ከሆነ ምንድ ነው ያነበበው ?(ሀገራዊ ጥያቄ ነው የጠየኳችሁ!)  

በተለይ ደሞ "ጥበብ ጠራችኝ ። ጥበብ አባረረችኝ።" በምንል በስነፅሁፍ ሰዎች መሐል ያለው መገፋፋት ፣ ምቀኝነት ፣ ክፉ ቅናት ፣ መናናቅ ፣ አንዱ አንዱን ለመጣል የሚደረግ ሴራ ፣ እብሪት የትየለሌ ሻጥሮች በኛ ላይ ይብሳል። 

እርግጥ ነው እጅግ በጣም ጥቂቶች በጣት የሚቆጠሩ የጥበብ ሰዎች ፣ ገጣሚዎች ፣ደራሲዎች ፣ ሰዓሊያን ከቅንነት እና ከእውቀት ጋር የሚኖሩት። በተረፈ አብዛኞቻችን እንጭራለን እናነባለን ፣ተምረናል ፣ አውቀናል የምንል የስነፅሁፍ ሰዎች ሲበዛ ምቀኞች ሴረኞች ፣ ክፉ ቅናተኞች ፣ እብሪተኞችና ስስታሞች ነው። 

አንዳንዱማ ላይክ ሲበዛልህ ካየ ፣ ስምህ በሰናይ መልኩ ሲነሳ ካየ አይኑ ደም ይለብሳስ !!! ታዲያ አንዳንዴ እናነባለን ፣ እንፅፋለን ፣ ተምረናል በምንለው ላይ ይህ ነገር ጎልቶ ሲታይ "ያልተማረ ይግደለኝ!" ያስብላል። 

አንዳንዴም "ምነው ጥበብ ስትጠራኝ የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው።" ባልኳት ኖሮ እያስባለ ያስቆጫል!!! አንዳንዴም ብዙ አንብበናል የምንል እኛ ምን እንዳነበብን ግራ ሲገባነ "መፅሐፍ ራሱን አያነብም!!!"ብለን እንፈላሰፋለን። ምን ይሆን የምናነበው?

በ"ኛል "ቤት መመካት

ሰው ዛሬ ቢወደኝ ፣ ነገ ይጠላኛል
ሳገኝ የቀረበኝ ፣ ሳጣ ይርቀኛል
አንድ እውነት ግን አለኝ!
ለፀብ ሲፈልጉኝ ፣ ፍቅር ያገኘኛል
እኔ አልታገልም
ጠልተው ሲታገሉኝ ፣ ፍቅሩ ይጥልልኛል
እርሱ ስለኳለኝ ፣ ማን ያጠለሸኛል ?!!!

መልካም የጡት ዘመን

እኔ ጡትሽ ሞኙ
እኔ ጡት አማኙ
እኔ በጡት ሟቹ ፣ እኔ በጡት ዳኙ

እኔ ጡት አምላኪው
ስለ ጡት ሰባኪው
ለጡት ተንበርካኪው

ከእናቴ ማህፀን...
ገና እንደወጣሁ ፣ የማውቃት ጣዕሜ
ከመዳህ አንስቶ...
ሒድ ብሎ ያቆመኝ ፣ ጡት ነውና አቅሜ
ጡት ስላለሽና
ጡት ስለመሰልሽኝ ፣ ወደድኩሽ ዓለሜ😂

እኔ ጡትሽ ሞኙ
እኔ ጡት አማኙ
እኔ ጡት ለማኙ

ልጅ ሳለሁ እናቴ...
ጡት አስጥል ቀብታ ጡቷን ስታስጥለኝ
መስከረም ሲጠባ ጡት እየመሠለኝ
ነጋ ጠባ ሲባል ጡት እየመሠለኝ
የተራሮች ጫፍ ጡት እየመሠለኝ

የሚጠባ እና..
የሚወርድ ነገር ጡት እየመሠለኝ
እንዳልሁሽ መሠረት
ጡት ለሚባል ነገር ታላቅ ፍቅር አለኝ ::

ይኸው ከዛ ወዲህ
ለጡት ያለኝ ፍቅር ፣ ስለነሳኝ አቅሌን
አደባባይ መሐል
ሐውልት አሰርቼ ፣ ያቆምኩት አኖሌን😂

እኔው ራሴው ነኝ
ሀገር ይወቅልኝ ፣ ለጡት መማለሌን😂

ይኸው ከዛ ወዲህ
እንደ ሀመሮች ጡት
ይቆማል ጆሮዬ ፣ ስለጡት ሲያወሱ
ግጥሜን አንብቤ
ከመድረክ ደረት ላይ
በወረድኩኝ ቁጥር ፣ ጡት ነኝ እኔ ራሱ😀

ይኸው ከዛ ወዲህ ወፈርኩ ስትዩኝ
አጋትሽ ነው ምለው ጡት ስለምትመሥዪኝ :)

በማየው ነገር ላይ ፣ ጡት እየተሳለ
ተራራው በሙሉ ፣ ጡት እየመሰለ
አይንሽና ጥርስሽ
መልክ ደምግባትሽ

ጡት መስሎ ቢታየኝ ፣ ወደድኩሽ በፍቅር
ጡት ባይኖርሽና...
ጡት ባትመስዪኝ ኖር ፣ አልወድሽም ነበር፡፡
ጡት ነው ምልክቴ
ጡት ነው ሐይማኖቴ

ጡት ነው የሚያሳየኝ ፣ የአይኔ ጨረሩ
ጡት ነው የሚመስሉኝ ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ
ጡት ነው የሚመስሉኝ ፣ ቅጠሉና ሳሩ፡፡

በቃ እኔ ጡት ስወድ...
እንደመስከረም ወር ፣
ሁሌ በያመቱ ፣ መጥባት ነው እቅዴ
ለጡት ካለኝ ፍቅር
ሁሌ ህፃን በሆንኩ ፣ እላለሁ አንዳንዴ
ከንፈርሽ ራሱ
ጣእሙን ስቀምሰው ፣ ጡት ጡት ይላል ውዴ፡፡

ደመናን ያጋተ ፣ ይህ ግዙፍ ሰማይም
መላኢክት ሚጠቡት...
ግዙፍ ጡት ይመስላል ፣ ጫፉ ባይታይም😀😀😂

መልካም አዲስ አመት ለሁላችሁ ከ❤ ተመኘሁ!!! 

ከወዲሁ ልሰናበት። የጡት ሰው ይበለን!!!

ሜድትራንያን ባህር የቀረው የስደተኛው ደብዳቤ ለድሀይቱ እናቴ


ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ - ፈላስፋዉ ጭሰኛ


አንተ ያለህ የሚገባው ፣ የለህም ለምን እንደሚሉህ ግራ የሚገባው፣ ትንሽ ሆነህ የመታየትህ ምክንያት በግብዳው የተረዳ ፣ ስታገኘው ጫና የምትሆንበት ፣ ስትለየው ሁልጊዜ የምታስበው፡፡ የህሊና እዳ የሚሆንብህ ፣ ልዩነትህን ለራሱ ድምቀት የሚጠቀም፣ ከሰው መሀል የሚሆነው ብቻውን እንዳይሆን ነው፡፡ ግርግር ለዚህ ሰው ሸከም ነው፡፡ ባያውቅህም ከተግባባህ ጓደኛው ነህ፡፡ የአስተሳሰብ ወንድምነት እንጂ የስጋ ዝምድና አይወድም፡፡ አለኝ ብሎ አክባሪ አይፈልግም፡፡ ብታከብረው የማይጎርር፣ ብትሰድበው የማይቀየም ፣ ብታከብረው ባታከብረው ስሜቱ አይለወጥም፡፡ ምንም ብትለው አይሰማውም ምክንያቱም የስሜቱ ምንጭ ራሱ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ በጣም የበሰለ

ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ......

የስጋ ምቾቱ ከነፍስ ስቃይ ያላዳነው ፣ በስጋው የተመቸው ፣ በነፍሱ የሚሰቃይ ፣ ያለቦታው በስህተት የተገኘ ፣ ሁልጊዜ ጥበብ የሚርበው ፣ የቁስ ኑሮ የታከተው፣ አለማወቁን አለማወቁ የሚቆጨው ፣ ጊዜ አስገድዶት የቁስ ሀብታም የሆነ ፣ ያለውን ንቆ የሌለውን የሚፈልግ፣ በቁስ መከበቡ የሚያስጠላው ፣ የሚወደው ጥበብ የሚያስጨንቀው ፣ የሚረዳህ ስላልገባው ነው፡፡ ለማስመሰል አይጠየቅም፡፡ የሚረዳህ ስላለው ሳይሆን ስለቸገረህ ነው፡፡ ችግር ለመፍታት እንጂ ካለው ለመቀነስ ሰጥቶ አያወቅም፡፡ ሊረዳህ ካልቻለ ራሱን የሚኮንን ፣ ለህይወቱ የአንተን ተሳትፎ ዋጋ የሚሰጥ ፣ በሰዎች ፊት ሲያከብርህ የማያፍር ፣ ሁልጊዘ ዝቅ ብሎ የሚያከብርህ የከፍታ ሰው ፣ አለ

ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ....

ትልቅ ለመሆን ተንጠራርቶ አያውቅም ፣ ባይንጠራራም ባለው ቁመት ትንሽ አይደለም፡፡ ለማሸነፍ ብሎ አይፎካከርም ፣ የሚወዳደረው በሌላው ድክመት ሳይሆን በራሱ ብቃት ነው፡፡ ሀብታም የሆነው ድህ ስላለ ፣ ለጋሽ የሆነው የተቸገረ በመኖሩ አይደለም፡፡ ጥሩ ሆኖ ለመገኘት ሀይማኖት አይፈልግም፡፡ ሀይማኖተኛ የሆነ ለሰው ብሎ ሳይሆን ትንሽም ብትሆን ለቀረችው እምነቱ ነው፡፡ ሀይማኖቱን ብትተች እንደሰደብከው አይሰማውም፡፡ ብሔር ለመተችት የሚጀምረው ከራሱ ማንነት ነው፡፡ ትችትንና ራሱን ለያይቶ ያስቀመጠ ፣ በራስህ ስትቀልድ ፣ ካንተ ብሶ በራሱ ቀልዶ ጨዋታ የሚፈጥር ፣ ለቀልድ አንዱን አእምሮውን ፣ ለቁምነገር ሌላኛውን በብቃት የሚጠቀም፣ ብታወዛገበው የሚያወዛግብህ ፣ ለማበሳጨት የማትችለው፣ ስህተቱን ለመናገር የማትፈራው ፣ ለትልቅ ሰው የቀለለ ፣ለትንሽ ሰው የከበደ

ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ......

ደረቅ አይደለም፡፡ የሚዋሸው እውነት ለመናገር ፣ ትክክል የሆነው ላለመሳሳት ፣ የሚያገኘው ላላማጣት ነው፡፡ ለማግኘት ብሎ አግኝቶ አያውቅም፡፡ የሚለብሰው ብርድ እንዳይመታው እንጂ ተብለጭልጮ ለመኖር አይደለም፡፡ የሚበላው እንዳይርበው ነው፡፡ ለመወፈር ብሎ አይበላም፡፡የሚጠጣው ለመስከር ሳይሆን ጥምን ለማርካት ነው፡፡ የሚኖረው ላለመሞት ነው፡፡ መኖር ለዚህ ሰው ብርቅ አይደለም፡፡ ለመኖር ብሎ አያስብም፡፡ ምክንያቱም የሚኖረው ለማሰብ ነው እሱም ፈላስፋዉ ጭሰኛ ነው ፡፡

የራስ ትዝብት - ፈላስፋዉ ጭሰኛ


በህይወቴ በነበረው የኑሮ ሂደት በደመ ነፍስ ከፈጠርኳቸው የህይወት መርሆች በሌላው ዘንድ እንደ መጥፎ ቢታዩም ለኔ ግን ጠቅመውኛል፡፡ የምኖረው ህይወቴን ሆነ ብዬ በማዝረክረክ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ህይወት እኔ ጋር ሁልጊዜ አዲስ ናት ፡፡ ምክንያቱም ህይወቴን የማዝረከርከው አሮጌውን በድጋሜ አስተካክዬ አዲስ ነገር ለመፍጠር ነው፡፡ ከእውነት አንፃር አዲስ ነገር የለም፡፡ ሁሉም አስቀድሞ የተፈጠረ ነው፡፡ አዲስ ነገር በሌለበት አለም እየኖርን ግን በህይወት ለመቆየት አዲስ ነገር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ ህይወት ከሌለ ሊኖር የሚችለው ሞት ነው፡፡ ስለዚህ እንደመፍትሔ የወሰድኩት ሁል ጊዜ የምኖረው አንድ አሮጌ ህይወትን በማዘበራረቅ በተለያዬ መንገድ በማስተካከል ነው፡፡ ሁልጊዜ ገንዘብ ካለኝ ህይወት አስልቺ ነው፡፡ አስልቺ ከሆነ እየተሞትኩ ነው፡፡ ምክንያቱም እድሜ ማለት አመታት መጨመር ሳይሆን ብዙ አዳዲስ ህይወቶችን መኖር መቻል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ላለመሞት አዲስ ህይወት መኖር አለብኝ ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ማግኘት አሰልቺ ከሆነ ማግኘቴ ሲዘበራረቅ አጣለሁ ፡፡ ያጣሁትን ሳገኝ እንደገና አዲስ ህይወት እኖራለሁ፡፡ ያገኘሁትን ሳጣው እንደገና አዲስ ህይወት እኖራለሁ፡፡ እንግዲህ አለም አሮጌ ከሆነች አዲስ ህይወት ያለው የደስታና ስቃይ ቅንብር ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ኤፒከረሳወውያን እንደሚያምኑት ነገ ለመደሰት ዛሬን በስቃይ ትኖራለህ፡፡ እየቆጠበክ ካልኖርከው ደስታም ያልቃል፡፡ የዚህ ጊዜ ህይወት ትርጉም አልባ ሆኖ አስልቺ ይሆናል፡፡ ያለመኖርም ስሜት ይፈጠራል፡፡ ያለመኖሩ ስሜት ከንቱነት ነው፡፡ ሁሉም ነገር አሮጌ ሆኖ አዲስ ህይወት ሲጠፋ ሰው በቁሙ ይሞታል፡፡ ከንቱነት ይኼ ነው፡፡ በቁም ላለመሞት አዲስ ህይወት አስፈላጊ ከሆነ መንገዱ አንድ ነው፡፡ አሮጌውን እያዘበራረቁ በማስተካከል እንደ አዲስ መኖር፡፡
ደንታ ቢስ ነኝ፡፡ሰዎች ቸልተኛ መሆን እንደሌለብኝ ይመክሩኛል፡፡ ለምን የሚለው ላይ ግን የኔ አርጊውመነት ከነሱ የተሻለ ነው፡፡ የነሱ አርጉመንት ደንታ ቢስ ከሆንክ ትጎዳለህ ነው፡፡ የኔ አርጉመነት ደግሞ እስከአሁን ያልተጎዳሁት ደንታ ቢስ በመሆኔ ነው ፡፡ የሁሉታችንም መደምደሚያ አለመጎዳት ከሆነ ደንታ ቢስ የሆንኩት ላለመጎዳት ነው፡፡ በእርግጥም ቸልተኛ መሆኔ ከብዙ ጉዳት ጠብቆኛል፡፡ በደል በበዛበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ እየኖርኩ እንደተበደልኩ አይሰማኝም፡፡ ካልተሰማኝ አልተጎዳሁም፡፡ ክህደት የእምነት ማጠንከሪያ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ብኖርም መካዴ ክህደት አልሆነም፡፡ እያመንኩት የሚክደኝ ጋደኛ ቢኖር ለኔ ክህደት አይደለም፡፡ አደራውን ከበላ ለሱ ሸክም ፣ ለኔ ደግሞ ችግር የመገላገል ያህል ነው፡፡ እኔ እንደተካድኩ ስለማይሰማኝ ከስቃይ ነፃ ነኝ፡፡ የስሜት ሸከሙ ከባድ የሚሆነው አደራ ለሰጠ ሳይሆን አደራውን ለተሸከመ ነው፡፡ ቢጉዳኝም፣ ስሜቱን ካልፈጠርኩ አልጎዳም።
ገንዘብ ቢነጥቁኝ እንደተቀማሁ አይሰማኝም፡፡ ባጣ የማጣት ስሜት የለም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያም እንዳገኘሁ አይሰማኝም፡፡ ካልተሰማኝ አላጣውም፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሞራል ህይወት መኖር የምችልበት ሰፊ እድል ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ቅንጦት ስቃይ ሆነ፡፡ የሚያስደስተኝ በስቃይ ውስጥ በማለፍ የሚገኝ እርካታ ሆነና የሞራል ህይወት ለኔ ወይ የማልመጥነው ፣ ወይ የማይመጥነኝ ኑሮ ሆነ፡፡ በዚህ የተነሳ በደመ ነፍስ ያዳበርኩት ልማድ ምን ሆነ ?? ደስተኛ ህይወት ለመኖር በስቃይ ውስጥ ማለፍ፡፡ ስቃዩ ሲያቆም ደስተኛ ህይወት መጀመር , ደስተኛ ህይወት ሲያቆም እንደገና መሰቃየት …
ምንም የለኝም፡፡ ምንም የሌለኝ ከሌላ ሰው ስለተለየሁ አይደለም፡፡ ቢጠፋ ቢጠፋ እንደሌላው ሰው እንዳለው ሆኖ መታየት አያቅተኝም፡፡ ምንም የሌለኝ ግን ምንም ስለማልፈልግ ነው፡፡ አሁን ያለኝ ፈልጌው የመጣ አይደለም፡፡ ከመጣ በኋላ እኔ የፈለኩት ነው፡፡ ካልመጣ አልፈልገውም፡፡ እኔ ጋር ካልመጣ የማልፈልገው ደግሞ የማልፈልገውን ህይወት መኖር ስለማልፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ባይኖረኝ ድሃ እንደሆንኩ አይሰማኝም፡፡ በመሰረቱ ድሃ የሚባል ሰው የለም፡፡ ሀብታም የሚባል ሰው የለም፡፡ ምክንያቱ፡ ድሀ የሚባል ሰው የለም፡፡ ሀብታምና ድሃ የሚል ክፍፍል የተፈጠረው በሰዎች የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ ሰዎች ከቁስ ሀብት ውጪ የሆነውን ሀብት መረዳት የሚችል ብቃት የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ዋጋውን መረዳት የቻሉት የቁስ ሀብት ያለው ሲሆን የሀብቱን ዋጋ መረዳት ያልቻሉት ደግሞ ድሃ ነው፡፡ ለሀብታሙ ዋጋ እንደሰጠነው ፣ ለድሀውም ዋጋ መስጠት ብንችል የሰው ልጅ በሙሉ ሀብታም ነው፡፡ በዚህ መሰረት ስለቸገረህ የሚሰጡህ ሰዎች መልካም ሰዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መቸገርህ መጥፎ ከሆነ እንዳትቸገር ማድረጋቸው መልካም በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተለዩ ሰዎች ደግሞ መኖራቸውን አስተዋልኩ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሆነ ነገር የሚሰጡህ ስለቸገረህ አይደለም፡፡ አንተ ጋር ያለውን ሀብት ትልቅ ዋጋ ሰጥተው ነው፡፡ የሚሰጡህ ምክንያት ስለቸገረህ አለመሆኑ ለምን መሰለህ ?? መጀመሪያም የቸገረህ ችግረኛ ስለሆንክ ሳይሆን የአንተን ሀብት ዋጋ መስጠት የሚችል ሰው ያለመኖሩ ችግር አስቸግሮህ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ቸግሮህ የሰጡህም መልካም ሰዎች ፣ ዋጋህ ገብቷቸውም የረዱህ ትክክለኛ ሰዎች ናቸው- መመስገን አለባቸው!