ሁለት ልጆቻቸው ወታደር ቤት ሄደው በመሞታቸው ምክንያት ጧሪ አጥተው ጎዳና ላይ የወጡትን እናት ፎቶ ትናንት ፌስ ቡክ ላይ ተለጥፎ አይቼ ነበር። ዛሬ መስከረም 5/2010 ዓ.ም ጎንደር ፒያሳ መንገድ ላይ ወድቀው እርዳታ የሚጠይቁ እናቶች መካከል ትናንት ፌስቡክ ላይ የተለጠፈውን የእርዳታ ወረቀት ድንገት አየሁት። የእርዳታ ጥሪውን ወረቀት ፊት ለፊታቸው ያስቀመጡት ቢያንስ 80 አመት የሚሆናቸው እናት የኢትዮጵያ ሆቴልን ግድግዳ ተጠግተው ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል። ሌሎች "የእኔ ብጤዎች" እንደሚያደርጉት አልፎ ሂያጁን አይለምኑም።
መጀመሪያ ከቤተሰብ ጋር ስለነበርኩ አልፌያቸው ከሄድኩ በሁዋላ ላናግራቸው ብቻየን ስመለስ መጀመሪያ እንዳየሁዋቸው አንገታቸውን ጉልበታቸው ላይ ደፍተው ተቀምጠዋል። እንዲሁ ለሚያያቸው የተኙ ቢመስሉም እንቅልፍ አልያዛቸው።ምን አልባት ሀገር እናስከብራለን ብለው እርሳቸውን ሳያስከብሩ የቀሩት ልጆቻቸውን ሀዘን አያስተኛቸው ይሆናል። ምን አልባት ርሃብ አያስተኛቸውም ይሆናል። ከጎናቸው ቁጭ ስል በደከመ አይናቸው ቀና ብለው ሲመለከቱኝ እንዳልተኙ ተረዳሁ። እርሃብ እና ሀዘኑ ተጨማምሮ እርጅና ተጫጭኗቸዋል። አይኖቻቸው ደክመዋል። ከመድከማቸው የተነሳ ሲያወሩ ድምፃቸው በደንብ አይሰማም።
ወይዘሮ ፈንታነሽ መለስ ጎንደር አይምባ አካባቢ በግብርና ይተዳደሩ ነበር። ባላቸው ከሞቱባቸው በሁዋላ ያለውና ሙቀት የተባሉት ወንድ ልጆቻቸው ይጦሯቸው ነበር። ሁለቱ ወንድ ልጆቻቸው "ሀገር ተወረረች" በተባሉት መሰረት ወላጅ እናታቸው ወይዘሮ ፈንታነሽን ብቻቸውን ጥለው የእናት ሀገር ዳር ደንበርን እናስጠብቃለን ብለው ባድመ ዘመቱ። ታላቁ ልጃቸው ሙቀት ክብረት በዚህ ጦርነት ሲሞት ሁለተኛው ልጃቸው ያለው ወረቀት ወንድሙ የሞተበት መሬት " የኤርትራ ነው!" ተብሎ ከተሰጠ በሁዋላ በቀረው ድንበር ተመድቦ ሲሰራ ቆይቷል።
ደርግ ሊወድቅ 3 አመት ሲቀረው የገበሬ ማህበር መሬታቸውን የነጠቃቸው ወ/ሮ ፈንታነሽ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝም መሬት አልባ ናቸው። መሬት ተከራይተው ሲጦሯቸው የነበሩት ልጆቻቸው ወታደር ቤት ከሄዱ በሁዋላ ይበልጡን ችግር ላይ ወደቁ።
ከጦርነቱ በሁዋላ ታናሹና በፎቶው ላይ የሚታየው መቶ አለቃ ያለው ወረቀት ከደሞዙ እየቆረጠ ይጦራቸው ነበር። ሆኖም መቶ አለቀ ያለው ወንድሙ የሞተበት ባድመ ማዶ የቀረው ድንበር ላይ ሲንከራተት በ"ብርድ በሽታ" ይታመማል። ይህ ነው የሚባል ህክምና ሳያገኝ ቆይቶ ህመሙ ሲብስበት ወደ ቤተሰብ ( ወደ እናቱ) ቀዬ ይልኩታል። ህመሙ ጠንቶበት ስለነበር ከተመለሰ ሁለት ቀን ሳይቆይ ብቸኛው ጧሪያቸው መቶ አለቃ ያለው ወረቀትም ይሞትባቸዋል።
መሬት አልባዋና ሁለት ልጆቻቸው "የእናት ሀገርን ዳርድንበር እናስጠብቃለን" በተባሉት መሰረት ጦር ሜዳ ሄደው የሞቱባቸው ወላጅ እናት ልጅ አልባ፣ ያለ ረዳት እና ጧሪ ይቀራሉ።ሄደው
ወ/ሮ ፈንታነሽ ይኖሩበት በነበረው ቀየ አጋዥ ሲያጡ የእርዳታ ጥሪው ላይ እንደሚሉት " ለወገን ደራሽ ወገን ነው" ብለው መንገድ ላይ ወድቀዋል። ቤተ ክርስቲያን እያደሩ ቀን ቀን ያችን የእርዳታ ወረቀት ዘርግተው አንገታቸውን ደፍተው መንገድ ዳር ይውላሉ። ኢትዮጵያውያን እናቶች እርዳት አጥተው መንገድ ላይ መውደቃቸው አዲስ ስላልሆነ ይመስላል አብዛኛው ሰው አንገታቸውን ደፍተው የተቀመጡትን እናት ከምንም ሳይቆጥር መንገዱን ይቀጥላል። የተወሰኑት ወረቀቱን አንብበው ከንፈር መጥጠው ያልፋሉ። በጣም ጥቂቶች ብቻ አስርም አምስትም ይጥሉላቸዋል። ከርሃብና ችጋር ባያድናቸውም።
ወ/ሮ ፋንታነሽ በተለይ ብቸኛው ጧሪያቸው መቶ አለቃ ያለው ከሞተ በሁዋላ ጡረታውን ለማስጠበቅ በዚህ እድሜያቸው "ይረዱሻል!" የተባሉትን መስርያ ቤት በሮች ቢረግጡም የልጆቻቸው ጡረታ ሊከበርላቸው አልቻለም።
በአሁኑ ወቅት የሀገርን ገንዘብ ለግላቸው ካካበቱ "ዘመነኞች" መካከል የመከላከያ አባላት(አዛዦች)ም እንዳሉበት ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ዳር ድንበርን ለማስከበር እየተባለ የአገዛዙን ስልጣን ሲያስከብሩ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለህዝብ ሳይሆኑ መጠቀሚያ ሆነው የሚያልፉት ብዙዎቹ ናቸው። እንደ ያለውና ሙቀት ያሉት የእናት ሀገር ዳር ድንበርን ለማስከበር ተብሎ የተዋጉለት ዳር ድንበር ጠላት ለተባለው ተሰጥቶ፣ ከሀገር ደህንነት ይልቅ ስልጣን ሲያስጠብቁ ህይወታቸውን ያጡ፣ አለቆቻቸው በሀገር ገንዘብ የግል ሆስፒታልና ሆቴል ሲሰሩ እነሱ በክሊኒክ ደረጃ ህክምና ያላገኙና ወላጆቻቸው ለርሃብና እርዛት የተዳረጉባቸው ሞልተዋል። ገዥዎች የመረጧቸው የመከላከያ አባላት (አዛዦች) የሀገር ንብረትን ከራሳቸው አልፈው ለሌላ መንደላቀቂያ ሲያደርጉ የደም ዋጋቸው ለወላጅ እናታቸው መጦሪያ አልተሰጠም። ጊዜ የሰጣቸው በሀገር ገንዘብ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውንን ሀብታም ሲያደርጉ፣ በተቃራኒው ለባለጊዜዎቹ መጠቀሚያ እንዲሆኑ ብቻ የተመረጡት እናቶች ወልደው ልጅ አልባ፣ ጧሪ አልባ ሆነዋል። እንደ ወይዘሮ ፈንታነሽ መለስ!
No comments: