Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » "ዝም አልልም፤ ለምን ዝም እላለሁ"፡ አና ጎሜዝ - ቢቢሲ

አና ጎሜዝ

ጥያቄ፡- ሰሞኑን አቶ በረከትን ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸው ነበር። 'ወ/ሮ አና፣ 'እባክዎ አርፈው ይቀመጡ' ብለዎታል፡፡ እንዲያውም እኚህ ሴትዮ ‹‹የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት አስተሳስብ አልለቀቃቸውም››፤ ሲሉ ነው አስተያየት የሰጡት።
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ለእንዲህ ዓይነት የወረደ ሐሳብ መልስ መስጠት አልሻም ነበር። አገሬን መስደባቸው ግን ትክክል አይደለም። እኔን እና አገሬን ከቅኝ ግዛት ጋር ማያያዛቸውም አሳፋሪ ነው። በፖርቹጋል እኔ የምታወቀው በጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎዬ ነው። ያውም ቅኝ ግዛትን መጻረር ፈታኝ በሆነበት ዘመን ነው የምልህ። 


ሕይወቴንም አደጋ ላይ ጥዬ ነው ይሄን ያደረገኩት። ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ነው ይሄን ተጋድሎ የፈጸምኩት። ታሪኬ የሚያስረዳውም ይህንን ነው።

ጥያቄ፡- ሁለታችሁን እንዲህ የቃላት ጦርነት ውስጥ የሚከታችሁ እኛ የማናውቀው ነገር አለ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ነገሩ በ2005 እኔ የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢ ቡድንን መምራት በጀመርኩበት ጊዜ የሆነ ነው። እሱ ያኔ የመንግሥት ተወካይ ነበር። ከእኔና እኔ ከምመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጋር እሱ ነበር በየጊዜው የሚገናኘው። የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትርም ነበር። በዚያ የታዛቢ ቡድን አማካኝነት እኔና የቡድኔ አባላት የተደረገውን ማጭበርበር ስላጋለጥን ነው በእኔ ላይ ቂም ይዞ የቆየው።

ከበረከት ስምኦን ጋር በጁን 8፣ 2005 የነበረንን ንግግር መቼም አልረሳውም። በመሐል አዲስ አበባ የተደረገውን ግድያ ሰምቼና ሆስፒታሎችን ጎብኝቼ ወዲያውኑ አገኘሁት። የጎበኘኋቸው ሐኪሞችና ነርሶች እያለቀሱ ነበር [በጥይት የተመቱትን] የሚያክሙት፡፡ 

ሁኔታው አስቆጥቷቸው ነበር። ባየሁት ጉዳይ ላይ መግለጫ እንደምሰጥ በረከትን ነገርኩት። እርሱ በዚህ ውሳኔዬ ተበሳጨ፡፡ ይባስ ብሎ ለተፈጠረው ግድያ ተጠያቂው የአውሮፓ ኅብረት ነው አለኝ። ይህ ብሽቅ የኾነ ሐሳብ ነው።
ጥያቄ፡- በቀደም ለታ የትዊተር ገጽዎ አቶ በረከትን ‹‹ርህራሔ የሌለው፣ ዋሾና፣ ጨካኝ›› ብለውታል። አልበዛም? የተጠቀሟቸው ቃላቶች የዲፕሎማት ቋንቋ አይመስልም።ወይዘሮ አና ጎሜዝ፦ እውነት ስለሆነ ነዋ፣ እውነት ስለሆነ ነው፥ እርሱ ጨካኝና ውሸታም ነው። በ2005 በደንብ አውቀዋለሁ ሰውዬውን። ባህሪው እንደዚያ ነው። እኔ ከአገሪቱ ጋር ምንም ችግር የለብኝም። የኔ ችግር ሁልጊዜም ከአምባገነኖች ጋር ነው።

ጥያቄ፡- አሁን ነገሩ ረዥም ጊዜ ሆነው እኮ፤ ለምን አይረሱትም ግን እርስዎ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ለምን እረሳለሁ?! በ2005ቱ ምርጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል። የነርሱ ቤተሰቦች ይህን የሚረሱ ይመስልኻል? ስለዚህ እኔም አልረሳም። የሰው ሕይወት ነው የጠፋው፤ ለግድያው ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ሰዎች አሉ፤ አንዱ አቶ በረከት ነው።

ይህን ጉዳይ የግለሰቦች ጉዳይ ለምን ታደርገዋለህ። እኔ በግል ከሰውየው ጋር ምንም ችግር የለብኝም እኮ። ፖለቲካዊ ነው ጉዳዩ። በርካታ ሰዎችን የጨፈጨፈውን ሥርዓት ሲያገለግል የነበረ ሰው ነው። እኔ ለማወቀውና ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ይሁን ነው እያልኩ ያለሁት። ብቸኛው ተጠያቂ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ሆኖም አንዱና ዋንኛው ነው።

ጥያቄ፡- ለማለት የፈለኩት ከእርስዎ ጋር ምርጫውን የታዘቡ፣ የኾነውን የተመለከቱ ብዙ ዲፕሎማቶች ነበሩ፤ አንዳቸውም በእርስዎ መጠን መንግሥት ላይ ትችት ሲሰነዝሩ አልሰማንም። እርስዎ ለምንድነው አንዲህ ነገሩን ለዓመታት የሙጥኝ ያሉት?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ዲፕሎማቶች የተፈጠሩት እንዲዋሹ አይመስለኝም። ዝም አልልም፤ ለምን ዝም እላለሁ፤ በመለስና በአቶ በረከት ትእዛዝ የተገደሉ ሰዎችን አይቻለሁ፤ ስለምን ዝም እላለሁ? አሁንም ላረጋግጥልህ የምፈልገው፤ አሁንም ወደፊትም ዝም አልልም።

ሌሎች ዝም ብለዋል ላልከው እኔ ያኔም ያስተጋባሁት የ200 የቡድኔን አባላት በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ያዩትን ነው። ያወጣነው ሪፖርት ደግሞ ከካርተር ሴንተር ካወጣው ሪፖርት ጋር የሚመሳሰል ነው። ነገር ግን ሁሉም ሰው ለአንድ ጉዳይ የሚሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። 

እኔ ባየሁት ነገር እጅግ ተቆጥቻለሁ። የመለስና የበረከት መንግሥት የሕዝብን ድምጽ ያጭበረበረበት መንገድ አናዶኛል። የአውሮፓ አገራት ይህንን መንግሥት እሹሩሩ ያሉበት መንገድ አበሳጭቶኛል።

አሁንም ዝም አልልም፤ ወደፊትም ዝም አልልም፤ በእጃቸው የሰው ደም ያለባቸውን እንደ አቶ በረከት ያሉ ሰዎችን በዝምታ አላልፋቸውም።

ጥያቄ፡- አቶ በረከት ወንጀለኛ ናቸው ለፍርድ ይቅረቡ እያሉ ነው?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ ፡- ይሄ ምን ጥያቄ አለው፤ አቶ በረከት ለፍርድ ነው መቅረብ ያለበት። እርግጥ ነው ብቻውን አይደለም፤ ግን ዋናው ሰው ነው፤ ለፍርድ የማይቀርበው ለምንድነው? አሁን ለውጥ ላይ ያለው መንግሥት ወደዚህ ድምዳሜ ላይ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ።

ጥያቄ፡- የአቶ በረከት ስምኦንን ጉዳይ ለጊዜው ገሸሽ እናድርገውና፤ ሌላ ጥያቄ ላንሳ፤ በ2012 አቶ መለስ ዜናዊ በብራስልስ መሞታቸውን ለኢሳት መረጃ ያቀበሉት እርስዎ ኖት እንዴ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ሊሆን ይችላል። መረጃው ነበረኝ። ያኔ ማንም መለስ ዜናዊ መታመሙን ቀርቶ አገር ውስጥ አለመኖሩንም የሚያውቅ ብዙ ሰው አልነበረም። መሞቱንም ብዙ ሰው አያውቅም ነበር። የነበረኝ መረጃ እጅግ አስተማማኝ የሚባል ነበር። ያን መረጃ ኢሳት የተጠቀመበት ይመስለኛል። ቀደም ብሎ መሞቱን የነገረኝ ምንጭ እጅግ የምተማመንበትና አስተማማኝ ነበር።

ጥያቄ፡- ስለዚህ አቶ መለስ የሞቱት በመንግሥት ከተገለጸው ቀን ቀደም ብሎ ነው ብለው በእርግጠኝነት መናገር ይችላሉ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ያለምንም ጥርጥር። መጀመርያ ብራዚል ለሕክምና ተወስዶ ነበር። ከሐኪሞቹ ጋር በብራዚል ተገናኝቷል። የሕመሙ ሁኔታ የተገመገመው ብራዚል በሚገኙ ስፔሻሊስቶች ነበር። ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ተነገረው። 

ከዚያ በኋላ ነው ብራስልስ እንዲመጣ የተደረገው። እኔ መረጃውን ባገኘሁበት ቅጽበት ራሱ ከቀናት በፊት መሞቱ ነው የተነገረኝ። ሆኖም በምሥጢር ተይዞ ነበር።

ጥያቄ፡- ትክክለኛ ቀኑን ያስታውሱታል?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- አላስታውስም
ጥያቄ፡- የትኛው በሽታ ለሞት እንደዳረጋቸውስ ያስታውሳሉ?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- እ…አንዳች የካንሰር ዓይነት ሕመም ሳይሆን አይቀርም፤ በትክክል ምን እንደነበር እርግጠኛ አይደለሁም።

ጥያቄ፡- መንግሥት ለምን መሞታቸውን ዘለግ ላለ ጊዜ መደበቅ የፈለገ ይመስልዎታል?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- እነርሱን ነው መጠየቅ ያለብህ። ነገር ግን በአምባገነን መንግሥታት ውስጥ የጠንካራ መሪ ሞት መደበቅ የተለመደ ነው፤ የመለስን ሞት ቀደም ብዬ አውቅ ነበር እያልኩህ አይደለም። 

እንደሰማሁት መረጃውን ሰጠሁ። ብዙም ሳይቆይ መንግሥትም መሞታቸውን አረጋገጠ። ከዚያ በፊት ግን ስለመታመማቸው እንኳን ለኢትዯጵያ ሕዝብ አልተነገረም ነበር።

ጥያቄ፡- እርስዎ መች ነው ግን ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የሰሙት?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- በልጅነቴ ነው። በቅኝ ግዛትና ከቅኝ ግዛትም በፊት በነበረው የአገሬ ታሪክ ወስጥ የኢትዮጵያ ስም ገናና ነው። ፖርቹጋሎች ለረዥም ዓመት ኢትዮጵያ በእግር ተጉዘው ለመድረስ ይሞክሩ ነበር። የፕሪስት ጆን አገር ተብላ ትታወቅ ነበር። የፖርቹጋል አሳሾች ትልቅ ጉጉት ነበራቸው፤ ይቺን አገር ለማየት።

እኔ አገሪቱን የረገጥኩት በ97 ምርጫ ጊዜ ነው። የያኔዋ ኮሚሽነር እኔን ወደዚያ እንድሄድ የመረጡኝ ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት ግንኙነት ከአገሪቱ ጋር ስላልነበረኝና ገለልተኛ ስለነበርኩ ነበር፤ በቆይታዬ አገሪቱን ተዘዋውሬ ሕዝቡንና ታሪኩን ስረዳ ይህ ሕዝብ ዲሞክራሲ ይገባዋል የሚል እምነት አድሮብኛል።

እኔ በአገሬ በጭቆና መኖሬ በጭቆና የሚኖር ሕዝብን እንድረዳ ረድቶኛል። ጨቋኞች ቋንቋቸው ይገባኛል። ዲሞክራሲ የሚል ቃል ያበዛሉ፤ ሽግግር ላይ ነን ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ከመለስ ጋር ረዥም ውይይትን አድርገናል።
ጥያቄ፡- ዘለግ ያለ ቆይታ ከአቶ መለስ ጋር ከነበርዎ አቶ መለስን ያውቋቸዋል ማለት ነው፤ አቶ መለስን እንዴት ይገልጿቸዋል?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ብልህ አጭበርባሪ (Deviously smart) ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳልዎ ይታማሉ፡፡ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- (ዘለግ ካለ ሳቅ በኋላ) ይሄ ፌዝ መሆን አለበት። ብርሃኑን አውቀዋለሁ። ባለቤቱን ዶክተር ናርዶስም አውቃታለሁ። ኢትዮጵያ እያለሁ ነው የማውቃት። 

እሷም ታውቃለች። አሁን የምነግርህን ታሪክ እሷ ራሱ ልትነግርህ ትችላለች። በ2005፣ ጁን 7 ሌሊት ጁን 8 ሊነጋ የኾነ ታሪክ ነው፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር የነበሩት ቲም ክላርክና ባለቤቱ ቤት ነው ያደርኩት። ያኔ የኔን የሸራተን መኝታ ለብርሃኑ ነጋ ለቅቄ ነው የሄድኩት። ለርሱ ብቻ አይደለም። ባለቤቱም ጭምር። ምክንያቱም ይህን ያደረኩት አደጋ ላይ ስለነበሩ ነው። ሌላ ቦታ ተደብቀው ነበር። 

የት እንደነበር አሁን አልነግርህም። የተሸሸጉበት ቦታ በመለስ ወታደሮች ሊታሰስ እንደሆነ መረጃ ለአምባሳደር ቲም ደርሶት ነበር። በአምባሳደር ቲም ክላርክና ባለቤቱ ጥያቄ መሠረት የሸራተን ክፍሌን ለብርሃኑና ባለቤቱ ለቅቄላቸዋለሁ።
ጥያቄ፡- ይህ ደርጊትዎ በራሱ በወቅቱ እርስዎ ገለልተኛ እንዳልነበሩ የሚያሳይ አይመስልዎትም?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡-  በፍጹም! በፍጹም! ሕይወቱ በአምባገነኖች አደጋ ላይ ላለ ለማንኛወም ሰው ላደርገው የምችለውን ነገር ነው ያደረኩት። የዶ/ር ብርሃኑና ባለቤቱ ሕይወት እኮ አደጋ ላይ ነበር። ለዚያም ነው አምባሳደር ቲም ክላርክ እኔ ክፍል እንዲቆዩ የፈለገው።

ጥያቄ፡- ብርሃኑን ካነሳን ዘንዳ ወደ ኤርትራ በረሃ መውረዱን ያደንቁለታል?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ለኔ ሊታገል አይደለም እኮ እዚያ የሄደው፤ ሰዎች ሲገፉ የት ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ እረዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ አምባገነኖች ላይ ነፍጥ ማንሳት ሊያስፈልግ ይችላል። ማንዴላም አሸባሪ ሲባሉ ነበር። 

በሰላማዊ ትግል ነው የማምነው፤ ኾኖም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፥ ምንም አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ይህ ሊሆን እንደሚችልም እረዳለሁ።
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያዊ ስም እንዳልዎ ያውቁ ይኾን?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- አዎ ብዙ ሰዎች ብዙ ስም እንዳወጡልኝ አውቃለሁ። በዋናነት «ጎቤዜ» የሚባለውን ሰምቻለሁ (ሳቅ)

ጥያቄ፡- ምን ይሰማዎታል ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- የሚያኮራ ነው። ሆኖም እኔ ከኢትዮጵያ ጋር የምጋራው ህልምና የሚያኮራኝ ነገር ካለ አንድ ነገር ነው፤ እሱም አገሪቱ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ተሸጋግራ ማየት።

ጥያቄ፡- አንዳንድ ቦታ ሰዎች የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፍ ሲወጡ የርስዎን ምሥል መያዝ ጀምረዋል።
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ምን ልበልህ …አመሰግናለሁ ስለ እውቅናው፤ ግን በሆነ መልኩ ደግሞ ኃላፊነትም ጭምር ይሰጣል። ስለ ዲሞራሲ ከሚታገሉ ሰዎች ጋር የኔን ምሥል ማየቴ ኢትዮጵያዊያንን በማገዝ እንድገፋበት ነው የሚያደርገኝ፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሩ ጅምር ላይ ያለ ይመስላል፤ ነገር ግን አስተማማኝ መሠረት ላይ ገና አልተቀመጠም።
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያዊ ዜግነት የመጠየቅ እቅድ ይኖርዎ ይሆን? ወይም ደግሞ የጡረታ ዘመንዎ በኢትዮጵያ የማድረግ ሐሳብ…ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ሳቅ- የኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ። ኾኖም የምትለው ዕቅድ የለኝም፤ ራሴን የማየው እንደዚያ ነው። እኔ ራሴን አንድ የዓለም ዜጋ አድርጌ ነው የምቆጥረው
ጥያቄ፡- በግልዎ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግና እንደሆኑ ይሰማዎት ይሆን?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- እንደዚያ እንደማላስብ ነግሬሀለሁ፤ አሁን የታየውን ተስፋ እንዲለመልም በጣም ተስፋ በማድረግ ላይ ነው ያለሁት።
ጥያቄ፡- ሳስበው ቤትዎ በኢትዮጵያዊ ቁሳቁሶች የተሞላ ይመስለኛል። ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- እውነትህን ነው፤ አሁን የማወራህ በብራስልስ ቢሮዬ ሆኜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራ አለ። በአንድ አርቲስት የተሳለ ቆንጆ የአዲስ አበባ ሥዕልም ይታየኛል፡፡ 

ቤቴም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ወዳጆቼ የሰጡኝ ማስታወሻዎች ይገኛሉ። በ97 ምርጫ የለበስኩት የምርጫ ታዛቢነት የደንብ ልብስም በማስታወሻነት አለ። በርካታ መስቀሎችም አሉኝ፡፡ ከመርካቶ የገዛኋቸው።

ጥያቄ፡- ወደ አቶ በረከት ጉዳይ አንድ አፍታ ልመስልዎ። ሰሞኑን በአማርኛ መጽሐፍ ጽፈዋል። የሚተርጉምልዎ በጎ ፈቃደኛ ቢያገኙ የማንበብ ፍላጎት አለዎ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ብዙ የምሰራቸው ቁምነገሮች አሉ። ብዙ ማንበብ ያለብኝ መጽሐፍት አሉኝ። ለምን ብዬ ነው ዋሾ ነው ብዬ የማምነው ሰው የጻፈውን መጽሐፍ የማነበው። የፕሮፓጋንዳ ፋብሪካ ነው እኮ እሱ። ምናልባት ወደፊት ሥራ ፈት ብሆን ላነበው እችል ይሆናል።

ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሚያደርጉት የበዛ ተሳትፎ…
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- የበዛ አትበል። የበዛ ነው ብዬ አላምንም።
ጥያቄ፡- …… በዚህ ተሳትፎዎ የሚበሳጩ ሰዎች የሉም?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ኦ! ብዙ ስድቦችንና ማንቋሸሾች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ይደርሱኛል። ከመንግስት ሰዎች ግን እንዲያ ያለ ነገር ዐይቼ አላውቅም። እዚህ ብራሰልስ የማገኛቸው ዲፕሎማቶች በመከባበር ነው የሚያወሩኝ። 

በ2013 አዲስ አበባ ሄጄ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምሳ ጋብዘውኛል። ሌሎችንም አግኝቻለሁ። የተለየ ነገር አላየሁም። ግለሰቦች ግን ይሳደባሉ። መለስ ዜናዊም ‹‹በኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ያን ሁሉ ገጽ ከተቃዋሚ ብር ትቀበላለች ብሎ ሰድቦኛል፡፡

ጥያቄ፡- ወደ አዲስ አበባ የመምጣት ፍላጎት አለዎት?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ብዙ ወዳጆቼ ለውጡን ተከትሎ እንድመጣ ይጠይቁኛል። ለመሔድ ብዬ አልሄድም። የማግዘው ነገር ሲኖር ያን አደርጋለሁ፤ ሰሞኑን ለምሳሌ ስቶክሆልም ባሉ ኢትዮጵያዊያን ለውይይት ተጋብዣለሁ። እሄዳለሁ።
ጥያቄ፡- ዐብይ አህመድን አግኝተዋቸዋል?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- አላገኘሁትም። እስክንድር ነጋን ግን አግኝቼዋለሁ። በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
ጥያቄ፦ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- መገምገም የምችለው በማገኛቸው ሰዎች ዐይን ነው። ለምሳሌ አንዳርጋቸው ጽጌ እዚህ አውሮፓ ኅብረት ምስክርነት ለመስጠት መጥቶ አግኝቼዋለሁ።  

ከዐብይ አሕመድ ጋር ቆይታ እንዳደረገ ነግሮኛል። አሱ በዐብይ ላይ ባሳደረው ተስፋ ተደንቂያለሁ። ለዲሞክራሲ ሕይወታቸውን የሰጡ ሰዎች ዐብይ ላይ ተስፋ ካሳደሩ እኔ ተስፋ የማላደርግበት ምክንያት የለም።

ጥያቄ፡- ተቃዋሚዎች ሥልጣን ቢይዙም ድምጾትን ማሰማቱን ይቀጥሉበታል?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- አዳምጠኝ፤ እኔ በኢትዮጵያ ጉዳይ ኤክስፐርት አይደለሁም። ባየሁት በደል ነው የተነሳሳሁት፥ የዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ለኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉጉት ያሳየውን ንቀት ነው እዚህ ውሰጥ የከተተኝ። ያ ነው አጋርነቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳደርግ የሚያደርገኝ፡፡

እኔ ማንም ይሁን ማን ለኢትዮጵያ ደሞክራሲን የሚያመጣ ልቤን ያሸንፈዋል፡፡ በ97 ያየሁትን የማውቀው እኔ ነኝ።
ጥያቄ፦ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እጅግ የሚያደንቁትን አንድ ሰው ይጥቀሱ ቢባሉ ያ ሰው ማን ነው?ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- ብዙ አሉ እኮ! ለምሳሌ የኦሮሞ ወጣቶች ይሄን አመጽ የጀመሩት ጀግኖች ናቸው። ብዙ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን አጋጥመውኛል፤ እነ መረራ፣ እነ እስክንድር…

ጥያቄ፡- አንድ ነበር ያልኩዎት?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡- አንድ ጀግና የለም። ዲሞክራሲ በአንድ ሰው አይገነባም። ብዙ ሰዎች ናቸው የሚገነቡት። እነ አንዳርጋቸው፣ ደግሞ ብርቱካን ሚደቅሳ ድንቅ ሴት ናት። የማይታወቁ ስንት ወጣቶች አሉ። ዐብይ የሚባለውን ሰው መቼ አውቀው ነበር? ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነው ስለርሱ የሰማሁት፡፡

ጥያቄ፦ከፖርቱጋል ውጭ በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በአንዱ የመኖር ዕድል ቢሰጥዎ የት ይመርጣሉ?
ወይዘሮ አና ጎሜዝ፡-  ተመልከት! አሜሪካ እንደ ዲፕሎማት ስኖር ይህ ዓይነቱ ነገር (ግሪንካርድ) ይቀርብልኝ ነበር። እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ደስ አይለኝም። ፖርቹጋላዊት ሆኜ ኖሬ መሞት ነው የምፈልገው። ያ ግን ለሌሎችን አገሮች ከመቆርቆር አይከለክለኝም።

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply