የባለ ብሩህ አእምሮው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መንገላታት፣ መታሰር፣ መገለል፣ መገፋት፣ መክሳትና መጥቆር አይተን ታመናል፣ ሰምተን ልባችን ተሰብሯል። የሱ መንፈስ ግን ሁሌም አዲስ፣ ምንግዜም ጠንካራ በመሆኑ በፅናቱ ሌሎችን ያፅናናል።
በእስክንድር እግር ሳተናው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሞጋች ብዕሩን አንስቶ በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ ልቡ የተንቀለቀለውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ተካ።ነበልባል ብዕሩ በእውነት የተሞላ ነበርና ትንታኔው ቢለበልባቸው፣ ፅሁፉ ቢያሸብራቸው፣ በብዕሩ ተናግሮ ቢያሳድዳቸው ብርቱውን ጋዜጠኛ ተሜንም አሰሩት፣ ፈረዱበት ይህም አላረካቸውም በእስር ላይ እስር ሆኑበት፣ ይጨልምበት ዘንድ በጨለማ ቤትም ወረወሩት። ተሜ ጨለማ እንደማይገታውና እስር አላማውን እንደማያስተው አላወቁትም።
ግፍ ሲጠነክር፣ ምሬት ሲያይል፣ መገፋት ሲበዛ ሌላ ትንታግ ይወለድ ዘንድ ምክንያት ይሆናልና እነሆ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ ፖለቲከኛ ዳንኤል ሺበሺና ሌሎች ድንቅ የኢትዮጵያ አሌኝታዎች ተፈጠሩልን። ጋዜጠኛ ኤልያስ ከወራት እንግልት በኋላ ተፈታ፣ ጎልማሳው ፖለቲከኛ ዳንኤል ሺበሺ በቅርቡ ከእስር ይፈታል፤ ሌሎች በስቃይ ያሉትም ነፃነታቸውን እንደሚቀዳጁ ጥርጥር የለንም። ምክንያቱም ሁሉም ግፍ የወለዳቸው፣ መገፋት የፈጠራቸው ሀገር ወዳዶች ናቸውና።
ሲገፉ ስለ መጠንከር፣ ሲቀጠቀጡ ስለ መበርታት፣ በምርመራ ዱላ ገላቸው ሲመተር ስለፅናት የሚሰብኩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው ልናከብራቸው፣ በርቱ ልንላቸው እና ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።
በፍትህ አደባባይ እስክንሰበሰብ ድረስ ፅናትን ያበዛላችሁ ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምናለን።
No comments: