በዚህች አለም ለሁሉም ፍጡራን በቂ የሆነ ስፍራ አለ። ምድሪቱ ባለፀጋ ነች ለሁላችንም ትተርፋለች። አኗኗራችን ነፃና ውብ መሆን ይችላል ግን መንገዳችንን ሳትን፤ ስስት የሰውን ልብ መረዘ፤ አለምን በጥላቻ ከፋፈለ፤ ምኞት ደም መፋሰስ ውስጥ ከተተን። በፍጥነት መጓዝ ብንችልም በራሳችን ውስጥ ተቀብረናል፤ ብዙ መስጠት የሚቻለው ጥበባችን ፈላጊዎች አድርጎናል፤ እውቀታችን ተጠራጣሪ፣ ጉብዝናችን ጨካኝና ክፉ አድርጎናል፤ ብዙ አሳቢዎች ግን ስሜት አልባዎች ሆነናል።
በአሁን ጊዜ ከማሽን ይበልጥ ሰብዓዊነት፤ ከጉብዝና ይልቅ ደግነትና ሩህሩነት ያስፈልገናል። ያለነዚህ ብቃቶች ህይወት ቀውስ ውስጥ ትሆንና ሁሉንም እናጣለን።
በአሁኑ ጊዜ ሚሊየን ተስፋ ያጡ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ህፃናትና የእድሜ ባለፀጎች በሚያሰቃይና ንፁሃንን በሚያስር ስርዓት ተጠቂዎች ናቸው።
ለእናንተ ይህን ለምታነቡት እላችኋለሁ… ተስፋ እንዳትቆርጡ፤ የወረደብን መከራ ምንም አይደለም የሚያልፍ ስስት ነው፤ የሰው ልጅን እድገት የሚፈሩ ሰዎች ጭካኔ ነው፤ የሰዎች ጥላቻ ያልፋል፤ አምባገነኖችም ይሞታሉ፤ የወሰዱት ስልጣን ለህዝቡ ይመለሳል፤ እስከሞትንላት ድረስ ነፃነት መቼም አትቀርም።
ወታደሮች ሆይ እራሳችሁን ለጨካኞች አትሰው። ለሚያንቋሽሿችሁ፣ ባሪያ ላረጓችሁ፣ ህይወታችሁን ለሚመሩ፣ ምን እንድታስቡ፥ ምን እንዲሰማችሁ ለሚነግሯችሁ፣ ለሚበያራቁቷችሁ፣ እንደ ከብት ለሚነዷችሁ፣ ጥይት ለሚቀልቧችሁ፣ ለእነዚህ ሰዎች አትሰዉ!! የሰው ማሽኖች፤ መሳሪያ እራሶች፤ መሳሪያ ልቦች አይደላችሁም… ከብት አይደላችሁም… እናንተ ሰው ናችሁ… የሰብዓዊነት ፍቅር በእናንተ ውስጥ አለ… አትጥሉ! ፍቅር ያጡና ተፈጥሮ የሌላቸው ብቻ ናቸው የሚጠሉ።
ጓዶች…ለባርነት አትዋጉ ለነፃነት እንጂ። ቅዱስ ማርቆስ እንዳለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሰውነታችሁ ነው፤ በአንድ ሰው አይደለም፣ በቡድን አይደለም፣ በሁሉም ሰው… በእናንተ ውስጥ ነው። ሀይል የህዝብ ነው፤ መሳሪያ የመፍጠር፤ ደስታን የመፍጠር፤ ይህንን ህይወት ነፃ፣ ውብና የተሻለ የማድረግ ሀይል አላቹ። በዲሞክራሲ ስም ይህንን ሀይል እንጠቀምበት፤ በአንድነት አንድ እንሁን፤ ቅድስት ለሆነች ሃገራችን እንታገል።
ቀና ለሆነው ህዝባችን ቀና ለመሆን፤ የመስራት እድልን ለሁሉም ዜጋ ለመፍጠር፤ ለወጣቱ መፃኢ ተስፋ ለመቆም ቃል በመግባት ነው ጨካኞች ስልጣን ላይ የሚወጡት! ግን ዋሽተውናል፤ ቃላቸውን አልጠበቁም መቼም አይጠብቁም። አምባገነኖች ራሳቸውን ነፃ ያወጣሉ ህዝቡን ግን ባርያ ያደርጉታል። ቃላቸውን አፍርሰዋልና ያንን ቃል እኛው በእኛው ለማስፈፀም እንታገል፤ ሃገራችንን ነፃ ለማውጣት፤ ድንበራችንን ለማስከበር እንታገል፤ ስስትን
ለመጣል፣ ጥላቻንና አለመቻቻልን ለማስቀረት፣ በምክንያት ለተፈጠረች ሃገራችን ስንል እንታገል።
ጓዶች ስለነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ እኩልነትና ከምንም በላይ ስለቅዲስቷ ሃገራችን ስንል በአንድነት አንድ እንሁን።
No comments: