በህይወቴ በነበረው የኑሮ ሂደት በደመ ነፍስ ከፈጠርኳቸው የህይወት መርሆች በሌላው ዘንድ እንደ መጥፎ ቢታዩም ለኔ ግን ጠቅመውኛል፡፡ የምኖረው ህይወቴን ሆነ ብዬ በማዝረክረክ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ህይወት እኔ ጋር ሁልጊዜ አዲስ ናት ፡፡ ምክንያቱም ህይወቴን የማዝረከርከው አሮጌውን በድጋሜ አስተካክዬ አዲስ ነገር ለመፍጠር ነው፡፡ ከእውነት አንፃር አዲስ ነገር የለም፡፡ ሁሉም አስቀድሞ የተፈጠረ ነው፡፡ አዲስ ነገር በሌለበት አለም እየኖርን ግን በህይወት ለመቆየት አዲስ ነገር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ ህይወት ከሌለ ሊኖር የሚችለው ሞት ነው፡፡ ስለዚህ እንደመፍትሔ የወሰድኩት ሁል ጊዜ የምኖረው አንድ አሮጌ ህይወትን በማዘበራረቅ በተለያዬ መንገድ በማስተካከል ነው፡፡ ሁልጊዜ ገንዘብ ካለኝ ህይወት አስልቺ ነው፡፡ አስልቺ ከሆነ እየተሞትኩ ነው፡፡ ምክንያቱም እድሜ ማለት አመታት መጨመር ሳይሆን ብዙ አዳዲስ ህይወቶችን መኖር መቻል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ላለመሞት አዲስ ህይወት መኖር አለብኝ ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ማግኘት አሰልቺ ከሆነ ማግኘቴ ሲዘበራረቅ አጣለሁ ፡፡ ያጣሁትን ሳገኝ እንደገና አዲስ ህይወት እኖራለሁ፡፡ ያገኘሁትን ሳጣው እንደገና አዲስ ህይወት እኖራለሁ፡፡ እንግዲህ አለም አሮጌ ከሆነች አዲስ ህይወት ያለው የደስታና ስቃይ ቅንብር ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ኤፒከረሳወውያን እንደሚያምኑት ነገ ለመደሰት ዛሬን በስቃይ ትኖራለህ፡፡ እየቆጠበክ ካልኖርከው ደስታም ያልቃል፡፡ የዚህ ጊዜ ህይወት ትርጉም አልባ ሆኖ አስልቺ ይሆናል፡፡ ያለመኖርም ስሜት ይፈጠራል፡፡ ያለመኖሩ ስሜት ከንቱነት ነው፡፡ ሁሉም ነገር አሮጌ ሆኖ አዲስ ህይወት ሲጠፋ ሰው በቁሙ ይሞታል፡፡ ከንቱነት ይኼ ነው፡፡ በቁም ላለመሞት አዲስ ህይወት አስፈላጊ ከሆነ መንገዱ አንድ ነው፡፡ አሮጌውን እያዘበራረቁ በማስተካከል እንደ አዲስ መኖር፡፡
ደንታ ቢስ ነኝ፡፡ሰዎች ቸልተኛ መሆን እንደሌለብኝ ይመክሩኛል፡፡ ለምን የሚለው ላይ ግን የኔ አርጊውመነት ከነሱ የተሻለ ነው፡፡ የነሱ አርጉመንት ደንታ ቢስ ከሆንክ ትጎዳለህ ነው፡፡ የኔ አርጉመነት ደግሞ እስከአሁን ያልተጎዳሁት ደንታ ቢስ በመሆኔ ነው ፡፡ የሁሉታችንም መደምደሚያ አለመጎዳት ከሆነ ደንታ ቢስ የሆንኩት ላለመጎዳት ነው፡፡ በእርግጥም ቸልተኛ መሆኔ ከብዙ ጉዳት ጠብቆኛል፡፡ በደል በበዛበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ እየኖርኩ እንደተበደልኩ አይሰማኝም፡፡ ካልተሰማኝ አልተጎዳሁም፡፡ ክህደት የእምነት ማጠንከሪያ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ብኖርም መካዴ ክህደት አልሆነም፡፡ እያመንኩት የሚክደኝ ጋደኛ ቢኖር ለኔ ክህደት አይደለም፡፡ አደራውን ከበላ ለሱ ሸክም ፣ ለኔ ደግሞ ችግር የመገላገል ያህል ነው፡፡ እኔ እንደተካድኩ ስለማይሰማኝ ከስቃይ ነፃ ነኝ፡፡ የስሜት ሸከሙ ከባድ የሚሆነው አደራ ለሰጠ ሳይሆን አደራውን ለተሸከመ ነው፡፡ ቢጉዳኝም፣ ስሜቱን ካልፈጠርኩ አልጎዳም።
ገንዘብ ቢነጥቁኝ እንደተቀማሁ አይሰማኝም፡፡ ባጣ የማጣት ስሜት የለም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያም እንዳገኘሁ አይሰማኝም፡፡ ካልተሰማኝ አላጣውም፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሞራል ህይወት መኖር የምችልበት ሰፊ እድል ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ቅንጦት ስቃይ ሆነ፡፡ የሚያስደስተኝ በስቃይ ውስጥ በማለፍ የሚገኝ እርካታ ሆነና የሞራል ህይወት ለኔ ወይ የማልመጥነው ፣ ወይ የማይመጥነኝ ኑሮ ሆነ፡፡ በዚህ የተነሳ በደመ ነፍስ ያዳበርኩት ልማድ ምን ሆነ ?? ደስተኛ ህይወት ለመኖር በስቃይ ውስጥ ማለፍ፡፡ ስቃዩ ሲያቆም ደስተኛ ህይወት መጀመር , ደስተኛ ህይወት ሲያቆም እንደገና መሰቃየት …
ምንም የለኝም፡፡ ምንም የሌለኝ ከሌላ ሰው ስለተለየሁ አይደለም፡፡ ቢጠፋ ቢጠፋ እንደሌላው ሰው እንዳለው ሆኖ መታየት አያቅተኝም፡፡ ምንም የሌለኝ ግን ምንም ስለማልፈልግ ነው፡፡ አሁን ያለኝ ፈልጌው የመጣ አይደለም፡፡ ከመጣ በኋላ እኔ የፈለኩት ነው፡፡ ካልመጣ አልፈልገውም፡፡ እኔ ጋር ካልመጣ የማልፈልገው ደግሞ የማልፈልገውን ህይወት መኖር ስለማልፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ባይኖረኝ ድሃ እንደሆንኩ አይሰማኝም፡፡ በመሰረቱ ድሃ የሚባል ሰው የለም፡፡ ሀብታም የሚባል ሰው የለም፡፡ ምክንያቱ፡ ድሀ የሚባል ሰው የለም፡፡ ሀብታምና ድሃ የሚል ክፍፍል የተፈጠረው በሰዎች የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ ሰዎች ከቁስ ሀብት ውጪ የሆነውን ሀብት መረዳት የሚችል ብቃት የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ዋጋውን መረዳት የቻሉት የቁስ ሀብት ያለው ሲሆን የሀብቱን ዋጋ መረዳት ያልቻሉት ደግሞ ድሃ ነው፡፡ ለሀብታሙ ዋጋ እንደሰጠነው ፣ ለድሀውም ዋጋ መስጠት ብንችል የሰው ልጅ በሙሉ ሀብታም ነው፡፡ በዚህ መሰረት ስለቸገረህ የሚሰጡህ ሰዎች መልካም ሰዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መቸገርህ መጥፎ ከሆነ እንዳትቸገር ማድረጋቸው መልካም በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተለዩ ሰዎች ደግሞ መኖራቸውን አስተዋልኩ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሆነ ነገር የሚሰጡህ ስለቸገረህ አይደለም፡፡ አንተ ጋር ያለውን ሀብት ትልቅ ዋጋ ሰጥተው ነው፡፡ የሚሰጡህ ምክንያት ስለቸገረህ አለመሆኑ ለምን መሰለህ ?? መጀመሪያም የቸገረህ ችግረኛ ስለሆንክ ሳይሆን የአንተን ሀብት ዋጋ መስጠት የሚችል ሰው ያለመኖሩ ችግር አስቸግሮህ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ቸግሮህ የሰጡህም መልካም ሰዎች ፣ ዋጋህ ገብቷቸውም የረዱህ ትክክለኛ ሰዎች ናቸው- መመስገን አለባቸው!
No comments: