ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ - ፈላስፋዉ ጭሰኛ
አንተ ያለህ የሚገባው ፣ የለህም ለምን እንደሚሉህ ግራ የሚገባው፣ ትንሽ ሆነህ የመታየትህ ምክንያት በግብዳው የተረዳ ፣ ስታገኘው ጫና የምትሆንበት ፣ ስትለየው ሁልጊዜ የምታስበው፡፡ የህሊና እዳ የሚሆንብህ ፣ ልዩነትህን ለራሱ ድምቀት የሚጠቀም፣ ከሰው መሀል የሚሆነው ብቻውን እንዳይሆን ነው፡፡ ግርግር ለዚህ ሰው ሸከም ነው፡፡ ባያውቅህም ከተግባባህ ጓደኛው ነህ፡፡ የአስተሳሰብ ወንድምነት እንጂ የስጋ ዝምድና አይወድም፡፡ አለኝ ብሎ አክባሪ አይፈልግም፡፡ ብታከብረው የማይጎርር፣ ብትሰድበው የማይቀየም ፣ ብታከብረው ባታከብረው ስሜቱ አይለወጥም፡፡ ምንም ብትለው አይሰማውም ምክንያቱም የስሜቱ ምንጭ ራሱ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ በጣም የበሰለ
ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ......
የስጋ ምቾቱ ከነፍስ ስቃይ ያላዳነው ፣ በስጋው የተመቸው ፣ በነፍሱ የሚሰቃይ ፣ ያለቦታው በስህተት የተገኘ ፣ ሁልጊዜ ጥበብ የሚርበው ፣ የቁስ ኑሮ የታከተው፣ አለማወቁን አለማወቁ የሚቆጨው ፣ ጊዜ አስገድዶት የቁስ ሀብታም የሆነ ፣ ያለውን ንቆ የሌለውን የሚፈልግ፣ በቁስ መከበቡ የሚያስጠላው ፣ የሚወደው ጥበብ የሚያስጨንቀው ፣ የሚረዳህ ስላልገባው ነው፡፡ ለማስመሰል አይጠየቅም፡፡ የሚረዳህ ስላለው ሳይሆን ስለቸገረህ ነው፡፡ ችግር ለመፍታት እንጂ ካለው ለመቀነስ ሰጥቶ አያወቅም፡፡ ሊረዳህ ካልቻለ ራሱን የሚኮንን ፣ ለህይወቱ የአንተን ተሳትፎ ዋጋ የሚሰጥ ፣ በሰዎች ፊት ሲያከብርህ የማያፍር ፣ ሁልጊዘ ዝቅ ብሎ የሚያከብርህ የከፍታ ሰው ፣ አለ
ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ....
ትልቅ ለመሆን ተንጠራርቶ አያውቅም ፣ ባይንጠራራም ባለው ቁመት ትንሽ አይደለም፡፡ ለማሸነፍ ብሎ አይፎካከርም ፣ የሚወዳደረው በሌላው ድክመት ሳይሆን በራሱ ብቃት ነው፡፡ ሀብታም የሆነው ድህ ስላለ ፣ ለጋሽ የሆነው የተቸገረ በመኖሩ አይደለም፡፡ ጥሩ ሆኖ ለመገኘት ሀይማኖት አይፈልግም፡፡ ሀይማኖተኛ የሆነ ለሰው ብሎ ሳይሆን ትንሽም ብትሆን ለቀረችው እምነቱ ነው፡፡ ሀይማኖቱን ብትተች እንደሰደብከው አይሰማውም፡፡ ብሔር ለመተችት የሚጀምረው ከራሱ ማንነት ነው፡፡ ትችትንና ራሱን ለያይቶ ያስቀመጠ ፣ በራስህ ስትቀልድ ፣ ካንተ ብሶ በራሱ ቀልዶ ጨዋታ የሚፈጥር ፣ ለቀልድ አንዱን አእምሮውን ፣ ለቁምነገር ሌላኛውን በብቃት የሚጠቀም፣ ብታወዛገበው የሚያወዛግብህ ፣ ለማበሳጨት የማትችለው፣ ስህተቱን ለመናገር የማትፈራው ፣ ለትልቅ ሰው የቀለለ ፣ለትንሽ ሰው የከበደ
ደግሞ አንዳንድ ሰው አለ......
ደረቅ አይደለም፡፡ የሚዋሸው እውነት ለመናገር ፣ ትክክል የሆነው ላለመሳሳት ፣ የሚያገኘው ላላማጣት ነው፡፡ ለማግኘት ብሎ አግኝቶ አያውቅም፡፡ የሚለብሰው ብርድ እንዳይመታው እንጂ ተብለጭልጮ ለመኖር አይደለም፡፡ የሚበላው እንዳይርበው ነው፡፡ ለመወፈር ብሎ አይበላም፡፡የሚጠጣው ለመስከር ሳይሆን ጥምን ለማርካት ነው፡፡ የሚኖረው ላለመሞት ነው፡፡ መኖር ለዚህ ሰው ብርቅ አይደለም፡፡ ለመኖር ብሎ አያስብም፡፡ ምክንያቱም የሚኖረው ለማሰብ ነው እሱም ፈላስፋዉ ጭሰኛ ነው ፡፡
Tag: Amharic ህይወት እና ፍልስፍና
No comments: