‹‹መንግስት- አገርን፣ ቃና- ትዳርን›› እንዲል ሼህ ሁሴን ጂብሪል) - አሳዬ ደርቤ
በፊት፣ በፊት እያንዳንዱ ምሽት የራሱ የሆነ ልዩ ትዝታ ነበረው፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ያሳለፍኳቸውን ምሽቶች ስገመግማቸው ቃና ቴሌቪዥኗንና አፏን ባንድ ላይ ከፍታ ፍዝዝ ካለች ሴት ምስል ውጭ ትዝ የሚለኝ ነገር፡፡
እውነት እላችኋለሁ በዚህ ቻናል የተነሳ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ባለቤቴና ልጄ ጋር ያለኝ መስተጋብር አፈር ድሜ በልቷል ማለት እችላለሁ፡፡ እግዜር ደህና ያድርገኝ እንጂ ይሄ ‹በስባሳ› ቻናል የተመሰረተበትን ምናምነኛ ዓመትቱን ሲያከብር እኔም ከሚስቴ ጋር ስለ ኑሮዬ መማካከርና መወያየት ያቆምኩበትን ምናምነኛ ዓመቴን አብሬው አከብራለሁ፡፡
ባለፈው በአዲሱ ዓመት እሰራቸዋለሁ የምላቸውን ነገሮች በጽሑፍ ሳሰፍር አምሽቼ ‹‹ያንችስ እቅድ ምንድን ነው?›› በማለት ባለቤቴን ብጠይቃት ቡናዋን እያማሳለች ‹‹የጀመርኳቸውን ፊልሞች ከመጨረስ ውጭ ምን እቅድ አለኝ ብለህ ነው?›› በማለት ስትመልስልኝ ብስጭቴን እቃ በመስበር ለመግለጽ አስቤ ዓይኔን አቅበዘብዝ ጀመር፡፡ እናም ሰው ሁሉ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት በሚሸጋገርበት ‹‹የዋዜማ ቀን›› እኔ ከአንዱ ንደት ወደ ሌላ አይነት ንደት መሸጋገር ስለሌለብኝ ቴሌቪዥኑን ገልምጬ፣ ጀበናውን ገልምጬ፣ ስኒውን ገልምጬ፣ የስኒ ማስቀመጫውን አፈፍ አድርጌ እንክትክቱን በማውጣት… አቅሜን ባገናዘበ መልኩ ብስጭቴን ገለጥኩኝ፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር እኔ በልጄ እድሜ ላይ እያለሁ የአባቴንና የእናቴን ዝርያ እስከ ሰባት ቤት ድረስ እዘረዝር ነበር፡፡ የእኔ ልጅ ግን ‹‹አያትህ ማን ነው?›› ብላችሁ አትጠይቁት እንጂ ቃና ላይ የሚሞላፈጡ ተዋናዮችን ንገረን እስኪ ብትሉት አፉን እያኮላተፈ አንድ በአንድ ይዘረዝርላችኋል፡፡
በበኩሌ ይሄን ፋይዳ ቢስ ቻናል ባለቤቴ መመልከቷን እንድትተው ለማድረግ ያልሞከርኩት ነገር የለም፡፡ ‹‹አንዱን ዓመት የዛራና ቻንድራን፣ ሌለኛውን ዓመት የኤሊፍና ኦመርን መጋባት ስትከታተይ የራስሽን ትዳር እየናድሽ ነው›› በማለት በተደጋጋሚ ብነግራትም ንግግሬ ስሜት የሚሰጣት አልሆነም፡፡ ያም ሆኖ በዚህ ቻናል ፊልም ላይ እንደሚታዩት እርካሽ ቤተሰቦች ትዳሬን መበተኑ ቀላል ስላልሆነልኝ ቴሌቪዥኔንና ሳሎኔን ለእሷ በማስረከብ መሰንበቱን መርጫለሁ፡፡
በባለፈው ልክ እንደ'ኔ ሁላ ሚስታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማሸነፍ ያቃታቸው አንዳንድ የፓርላማ አባላት ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ይሄ በክት ቻናል እንዲዘጋላቸው የሚያሳስብ ጥያቄያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስንቱን ጋዜጣና መጽሄት በተቋቋሙ ማግስት ሲያከስም… እነ ቪኦኤን፣ ዶቾቬሌንና ኢሳትን ጃም ለማስደረግ በሚሊዮን ብር ወጭ ሲያደርግ… ህገ-መንግስቱን ዞር ብሎ አይቶ የማያውቀው ወመኔው መንግስታችን፣ ጥያቄው ቃና ላይ ሲሆን ይሄንን ማንነቱን ዘንግቶ ‹‹ቻናሉን ለማገድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ የለኝም›› ብሎ ጠያቂዎቹን በማኮናፈስ በቀን ሶስት ጊዜ ሊያበላው ያልቻለውን ሆደ-ሰፊ ህዝብ በቀን ሶስት ድራማ እንዲመለከት ፍቃዱን ሰጠ፡፡
እውነት ለመናገር ከመንግስት በኩል የተሰጠው መልስ የምጠብቀው ስለሆነ አላስገረመኝም፡፡ ከቀን ወደ ቀን እንደ እነሱ ቀፈት እየገዘፈ የሚመጣ ድህነታችንንና ከእለት ወደ እለት እየመነመነ የሚታይ ነጻነታችንን የሚያስረሳ፣ ቻናል ሲከፈት በበጄት እየደጎሙ ማጠናከር እንጂ ማቋረጥ አያስፈልግም፡፡
…ምንም እንኳን ይሄ እድፋም ቻናል ቤተሰባዊ መስተጋብርን የሚያጠፋ፣ በትዳር ላይ መማገጥን፣ ሚስትና ባል መነጣጠቅን የሚያስፋፋ፣ ያለንን ኢትዮጵያዊ ግብረ-ገብነትንና ጨዋነትን ከማክሰም በዘለለ ለህብረተሰቡ የሚበጀው አንዳች ነገር ባይኖርም ዓይናችንን ከቤታችንና ከአገራችን ላይ አንስተን ቱርክና ሜክሲኮ መሬት ላይ ማስቀመጣችን በመንግስት በኩል በጥብቅ የሚፈለግ ነው፡፡
…ምንም እንኳን ይሄ ቆሻሻ ቻናል የህብረተሰቡን አላዋቂነትና ጉድለት ተጠቅሞ የራሱን ጥንስስ እየጠመቀ ተመልካቹን ከመጋት ባለፈ… ስናዝን ቁዘማችንን የማይጋራ፣ ስንደሰት ደስታችንን የማይካፈል፣ ዓመት በዓል ስናከብር ደግሞ አውዳመታችንን የሚያደምቅ ምንም አይነት ዝግጅት የሌለው፣ ስለታሪካችንም ሆነ ስለ ሀይማኖታችን ግድ የማይሰጠው ቢሆንም… እኒህ ጉድለቶቹ ከመንግስት ጋር ሊያመሳስሉት እንጂ ሊያለያዩት አይችሉም፡፡ (‹‹መንግስት አገርን፣ ቃና ትዳርን›› እንዲል ሼህ ሁሴን ጂብሪል)
…ምንም እንኳን ይሄ ተልካሻ ቻናል እሱ ተርጉሞ ከሚያቀርባቸው ፊልሞችና ድራማዎች በጭብጥም ሆነ በቅርጽ የተሻሉ በሃገራችን ተዋናዮች የሚሰሩ ፊልሞችን- አፈር ያለበሰ፣ ከእሱ በፊት የነበሩትንም ሆነ ከእሱ በኋላ የመጡትን አማርኛ ቻናሎች በጥቁር መጋረጃው ጋርዶ በስንት ልፋትና ወጭ የሚያዘጋጇቸውን ፕሮግራሞች እራሳቸው አዘጋጆቹ እንዲመለከቱት ያደረገ ቢሆንም 25 ዓመት ሙሉ አንድ ቻናል እንድንመለከት ለፈረደብን መንግስታችን ይህ ጉዳይ ከመጤፍ የሚቆጠር አይደለም፡፡
እናም በአጠቃላይ የዚህ ቻናል መፈጠር ለመንግስታችን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር እንጂ ስጋት ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ቢያንስ የሃይማኖት አባቶች ቻናሉ ተማሪዎችን ከንባባቸው፣ ሚስቶችን ከባሎቻቸው የሚያለያይ፣ ምዕመናኑን ከትምህርት ቤትና ከቤተ-እምነት የሚያስቀር ስለሆነ…. በተባባረ ድምጻቸው አማኞቻቸውን ይሄን ቻናል እንዳይመለከቱ ሊገዝቷቸው ይገባል እላለሁኝ፡፡
Tag:
No comments: