Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » » » » » ይድረሰ ለአቶ ታዬ ደንደኣ “እንዴት የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብሩ ወደሚገፈፍበት ጦላይ ይላካል?” ስዩም ተሾመ

ለአቶ ታዬ ደንደኣ

ለአቶ ታዬ ደንደኣ
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር
አዲስ አበባ


ውድ ታዬ፣ የከበረ ሰላምታዬ ይድረስህ! እንደምን አለህ? በእርግጥ ይህን ደብዳቤ በይፋ ከመፃፍ ይልቅ በግል ላናግርህ እንደምችል አውቃለሁ።

ነገር ግን ይህን ለማድረግ ውስጤ አልፈቀደም። ምክንያቱም በማዕከላዊ እና ሦስተኛ እስር ቤቶች ውስጥ ብዙ ብዙ ነገሮችን ተጫውተናል። በእውነቱ ከአንተ ጋር መታሰር ትምህርት ቤት እንደ መግባት ነው። ከአንተ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ።

በተለይ ደግሞ በሀገራችን ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ለማምጣት፣ በዚህ የዜጎች መብትና እኩልነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ቀዳሚው ተግባር ፍትህ እና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ አለበት የሚል ፅኑ እምነት እንዳለህ አውቃለሁ።

ባለፈው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር በመሆን ስትሾም ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ያልሆንኩት ለዚህ ነው። ምክንያቱም ገና እስር ቤት እያለን “ታዬ አንተን ማየት የምፈልገው የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ወይም ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ዋና አቃቤ ሆነህ ነው” ብዬህ እንደነበር ታስታውሳለህ።

በእርግጥ እስር ቤት ውስጥ የተወያየንባቸውን ጉዳዮች በሙሉ አንድ በአንድ ታስታውሳለህ ብዬ አልጠብቅም። ነገር ግን ዕምባዬን እያፈሰስኩ በዝርዝር የነገርኩህን ነገር ግን የምትረሳ አይመስለኝም።

በማዕከላዊ እስር ቤት ከነበርኩበት ጣውላ ቤት ወደ “09” ወይም ሸራተን ተዛውሬ እንደመጣሁ “እስኪ ስለ ጦላይ ንገረኝ?” ብለህኝ ነበር። በ2009 ዓ.ም ከተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የመጡ ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎች “ጦላይ” በሚባል ምድራዊ ሲዖል ውስጥ ምን ዓይነት ግፍና በደል እንደ ተፈፀመባቸው በዝርዝር ነግሬህ ነበር።

ጦላይ ውስጥ ስለሆነው ነገር መናገር አልሻም። ጦላይ ውስጥ የታዘብኩትን አሰቃቂ እውነት ተመልሶ ማሰብ፣ በእኔ ላይ የደረሰው በደልና ሰቆቃ በፍፁም ማስታወስ አልሻም።

በዚያ የተረገመ ቦታ ያየሁትን ግፍና ሰቆቃ ስናገር ነፍሴ ትሰቃያለች፣ አንደበቴ በሲቃ ይዘጋና መናገር ይሳነኛል። ስለዚህ በቃላቶች ፋንታ ዕምባዬ ይፈስሳል። በውስጤ ታፍኖ ያለው መከራና ስቃይ በዕምባ መልክ ገንፍሎ ይፈስሳል።

አንደበቴ በሲቃ ተሞልቶ የጦላይን ስቃይና ሰቆቃ በዕምባዬ የምነግረው በጣም ለምቀርበው ሰው ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ታዬ አንተ ነህ። ይህን የነገርኩህ ደግሞ እንደ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ጦላይ ውስጥ ያንን አሰቃቂ ተግባር የፈጸሙ የኦሮሚያና ፌደራል ፖሊሶችን ለፍርድ ታቀርባለህ የሚል ፅኑ እምነት ስለነበረኝ ነው።

ምክንያቱም በወቅቱ የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስለነበርክ ብቻ ሳይሆን በፌደራል ደረጃ ትልቅ ቦታ እንደምትደርስ አውቃለሁ።

ከሁሉም በላይ ደግሞ “እዚህ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ቀዳሚው ተግባር ፍትህ እና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ነው” የሚል ፅኑ እምነት እንዳለህ አውቃለሁ።

ይሁን እንጂ አንተ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኃላፊ ሆነህ ሳለ ወደ አንድ ሺህ አራት መቶ (1400) የአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ጦላይ ተወስደዋል። እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ነገር ማለት አልፈልግም ነበር። ምክንያቱም አንደኛ፡- ውጪ ሀገር ስለነበርኩ በጉዳዩ ዙሪ ሙሉ መረጃ አልነበረኝም፣ ሁለተኛ፡- ይህ ተግባር በዕውን ይሆናል ብዬ ማመን አልቻልኩም።

ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ ነው። ለወታደራዊ ስልጠና ከሚላኩ ሰዎች በስተቀር ማንም ሰው ወደዚያ ቦታ መሄድ የለበትም።

ምክንያቱም ሰዎች ወደ ጦላይ የሚወሰዱት ለሰው ልጅ ክብርና ርህራሄ የሌላቸው ፍፁም ጫካኝ የሆኑ ፖሊሶችና ወታደሮች፣ ከዓለምና ከኢትዮጵያ ህዝብ እይታ ተሰውረው፣ መንግስትና ህግ በሌለበት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር ለመግፈፍ እንዲያመቻቸው እንደሆነ እኔ በተግባር አይቼዋለሁ።

ውድ ታዬ… የተጠቀሱት የአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ጦላይ እንዲላኩ አድርገሃል ብዬ እየወቀስኩህ አይደለም። በእርግጥ እንደ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ ጉዳዩ አንተን ይመለከታል።

ይሁን እንጂ እነዚህን ወጣቶች በራስህ ጦላይ ማስገባት ሆነ ማስወጣት እንደማትችል አውቃለሁ። ምንአልባትም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማድረግ አትችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ቁስሌ ሳይሽር፣ ዕምባዬ ሳይደርቅ እንዴት ሰው ወደ ጦላይ ይላካል?


ብዙ ምክንያት ልትጠቅስልኝ፣ ብዙ ነገር ልትነግረኝ እንደምትችል አውቃለሁ። የምትነግረኝ ነገር ግን ስለ ጦላይ የማውቀውን፣ እዚያ የተደረገውን እና የሚደረገውን ነገር አይቀይረውም። የሰው ልጅን ወደ ምድራዊ ሲዖል መላክ በምንም አግባብ፣ እንዴትም ሆኖ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

እንዴት ታዬ?? እንዴት እንዲህ ይደረጋል? እንዴት የሀገር ልጅ ወደ ጦላይ ይላካል? እንዴትና ለምን በእኛ ላይ የደረሰው በአዲስ አበባ ልጅ ላይ ይደገማል? ታዬ የክፉ ቀን ወዳጄ… እንዴት የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብሩ ወደሚገፈፍበት፣ ወደዚያ የተረገመ ቦታ ይላካል???? እንዴት……

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply