Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7

አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በሀገራችን የተፈጠረውን የለውጥ ሂደትን በመመርመር በትንተና ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ ለሕዝብ ሲያቀርብ ቆይቷል፤ የራሱንም ተግባራት በትንተናው ውጤት መሠረት ሲመራ ቆይቷል።

ይህ የለውጥ ሂደት ወደ እውነተኛና ዘላቂ ዲሞክራሲያው ሥርዓት እንዲያሸጋግረን ከመነሻው መሟላት አለባቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በግልጽ በማስቀመጥ አብዛኛዎቹ መሟላታቸውንና የተቀሩትን ደግሞ ለሟሟላት ተጨባጥ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ለመገንዘብ ችሎአል።

በዚህም የተነሳ ንቅናቄዓችን እስካዛሬ ለውጡ የሄደበትን ርቀት በማጤን በሀገር ውስጥ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል በማድረግ የተጀምረው የለውጥ ሂደት ወደ እውነተኛ ዘላቂ ለውጥ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ አለ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። 


ከዚህም ድምዳሜ በመነሳት ከዚህ በፊት ይታገልበት የነበረበትን የሁለገብ የትግል ስትራቴጂ በመፈተሽ በሀገር ውስጥ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፏል።

ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓም በውጭ የነበረው የንቅናቄዓችን አመራርና ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ በርካታ ነባር አባላት ወደ ሀገር ውስጥ በይፋ የሚገቡበት ምክንያትም ይህንኑ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችልና አገራችንን ፍትህ ፤እኩልነትና ነጻነት ወደ ሰፈነበት የዲሞክራሲ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ትግል ለማገዝ ካለው ጽኑ እምነት ነው። 

የንቅናቄያችንን ራዕይ የሚጋራው ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ሀገር ውስጥ የሚገኘው የንቅናቄው አካል ከውጭ የሚመጡትን አመራሮችና አባላት ለመቀበል በአዲስ አበባና በሌሎችም የሀገሪቷ ከተሞች ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ ያለውም ከዚህ አኳያ እንደሆነ እሙን ነው ። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ጵጉሜ 4 ቀን 2010 ዓም በሚደረገው የአቀባበል በዓል ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማው ሕዝብ ሊወጣ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።

አርበኞች ግንቦት 7፣ እጅግ አስቸጋሪ በነበሩ ዓመታት ከጎኑ ለቆሙ፣ በስሙ ለታሰሩ፣ ለተገረፉ፣ ለተገፉ ወገኖቻችን ሁሉ ምስጋና ያቀርባል፤ ለቀሪው ትግልም አብረን እንድንሳተፍ ጥሪ ያደርጋል። 

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ተጠቃሎ አገር ውስጥ የሚገባበት ይህ ቀን ጳጉሜ 4 / 2010 ዓም ለድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በሰለጠነ ሀገራዊ ፖለቲካ ለሚያምን ማንኛውም ዜጋ ትልቅ ዋጋ ያለው ኩነት እንደሆነ ንቅናቄው ያምናል። ይህም በመሆኑ የአቀባበሉ ሂደት ድርጅቱ የቆመለትን የሰለጠነ ሀገራዊ ፖለቲካ የሚመጥን የሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር ደረጃ የጠበቀ መሆን ይገባዋል።

በዕለቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የምንካፈል ዜጎች የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች አቀባበል ሀገራዊ አንድነትና መቀራረብ በሚያጎለብት መንገድ እንዲጠናቀቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዕለቱ ፍቅር፣ መደጋገፍና መቻቻል የሚጎለብቱበት፤ ጠላትነት፣ መራራቅንና መከፋፈል የሚሟሽሹበት ማድረግ ይኖርብናል።

በዚህም ምክንያት በዕለቱ ሥነ ሥርዓት ለማስከበርና የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ከተሰማሩ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ይህ ታሪካዊ የአቀባበል በዓል በተረጋጋ ሁኔታ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ አርበኖች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪ ያቀርባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናንቄ

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply