Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » እኛ እሹሩሩ የምንለው የዘር ፖለቲካን ዓለም ቆርጦ የጣለው ነቀርሳ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም!!

የዘር ፖለቲካን

ብንን ስል ከሃሳቤ
ያለምኩትን በ‘ውን አየሁ፣
መንፈሴ ውስጥ ውልብ ሲል
ከኔ ሌላ እኔ እንዳለሁ!


ሰውየው ብቻውን ነው የሚኖረው፡፡ ዘወትር ጠዋት ከመኝታው ሲነሳ ትላንት ያልሰራው ተሰርቶ፣ ትናንት ያላስቀመጠው ተቀምጦ፣ ትናንት ያልሆነው ሆኖ ይጠብቀዋል፡፡ … 

የአትክልት ቦታው ተኮትኩቶና አምሮ፣ ራቱን የተመገበባቸው ዕቃዎች ፀድተው፣ ወንበሮቹ በትክክል ተደርድረው፣ ተዝረክርኮ የነበረው ሁሉ በወግ በወጉ ሆኖ ያገኛቸዋል፡፡ … ግርም ይለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ … እንደው ለምናልባት በማለት “አመሰግናለሁ” የሚል ማስታወሻ ፅፎ ወደ ስራው ይሄዳል፡፡ … መልስ የለም፡፡  

ለጓደኞቹና ለስራ ባልደረቦቹ ሲነግራቸው … አንዳንዶቹ ቅዠት ነው፣ አንዳንዶቹ የሚወድህ ሰው መንፈስ ነው፣ አንዳንዶቹ ሰይጣን ነው … ወዘተ ይሉታል፡፡ ብዙዎቹ ግን ውሸቱን ነው ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ግራ የሚያጋባውና ጤንነቱን እንዲጠራጠር የሚያደርገው ደግሞ ጠዋት እላጨዋለሁ ብሎ ያሰበው ፂም ሙልጭ ብሎ ማደሩ ነው፡፡ 

በዚህ ሁኔታ ዓመታት እየመጡ፣ ዓመታት ተሸኙ። ሰውየው እንግዳ የሆኑበትን ነገሮች ለመዳቸው፡፡ … ማሰቡንም እየረሳው መጣ፡፡ አንድ ጠዋት ግን አዲስ ነገር አጋጠመው፡፡ … ትናንት ምሽት ወደ ቤቱ ሲመለስ ገዝቶ ባመጣው አዲስ የመፃፊያ ደብተር (writing pad) ላይ “ምዕራፍ አንድ” ብሎ የሚጀምር አጓጊ ታሪክ ተፅፎ ተመለከተና ደነገጠ፡፡  

የደነገጠው በተፃፈው ነገር ሳይሆን ታሪኩን ካሁን ቀደም የሚያውቀው ስለመሰለው ነበር፡፡ … ይህንንም ቢያወራ የሚያምነው ስለሌለ ዝም አለ፡፡ … ታሪኩም … ምዕራፍ ሁለት፣ ምዕራፍ ሶስት፣ አራት፣ አምስት እያለ … ከብዙ ወራት በኋላ ተጠናቀቀ፡፡ … ማን ይሆን እንዲህ የሚያደርገው?
***
“መኖርን አቁሜ መሆንን መርጫለሁ (I cease to live and begin to live) ያለውና ‹ሰላማዊ ሽፍታ› በመባል የሚታወቀው ሄንሪ ዳቪድዞሮ፤ ነፃነት ወይም ሞት (Give me liberty or give me death) ባዩ ፓትሪክ ሄንሪን ዓይነት የመብት ተሟጋቾች፤  

“ቅር የሚለኝ ነገር ቢኖር ለአገሬ የምሞተው አንድ ጊዜ ብቻ ነው (I only regrat that I have but one life to lose for my country) ያለው ናታን ሃሌን ዓይነት አገር ወዳድና ሌሎች ብዙ ድንቅ ዜጎችን አፍርታለች!! … የተባበረችው አሜሪካ!! … 

ከነዚህ ሰዎች ተርታ፣ የዛሬ ሰባና ሰማንያ ዓመታት ገደማ ሌላ ታላቅ የመብት ተሟጋችና የትውልድ ፋና ወጊ የሆነውን ታላቁን ማርቲን ሉተር ኪንግን ፈጥራለች፡፡ .. ይቺው የተባበረች አሜሪካ!!  

“ህዝባዊ ብሶት በሰላማዊ መንገድ እንዳይገለፅ ከታፈነ አመድ ሆኖ ይገነፍላል (… if repressed emotions are not released in non - violent ways, they will seek expression through violence, this is not a threat but a fact of history) … 

ይኸ ከታሪክ የተማርነው ሃቅ እንጂ ማስፈራሪያ አይደለም” በማለት ከበርኒንግሃም እስር ቤት በፃፈውና በሁዋላም በመፅሃፉ በተካተተው ደብዳቤ (a letter from Burningham prison) አገሩ እውነትን ፊት ለፊት እንዲጋፈጥ አዘጋጅቶታል፡፡ … ማርቲን ሉተር ኪንግ ጂኒየር!!

ሰውየው “ህልም አለኝ I have a dream!” በማለት በሊንከን ሜሞሪያል አደባባይ ያደረገው ልብ የሚነካ ታሪካዊ ንግግር እነሆ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን, 2018 ሃምሳ አምስተኛ ዓመቱ ተዘክሮለታል፡፡ 

የማርቲን ሉተር ኪንግ “Integrationism” (አግላይ ያልሆነ ወይም ተደማሪነት) …. የፖለቲካ ፍልስፍና እንደ ሌሎቹ ‹ጥቁር ብሄርተኝነት›ን መሰረት ያደረገ እንዳልነበር ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡- እ.ኤ.አ በ1965 ከማርቲን ሉተር ኪንግ ሶስት ዓመት ቀደም ብሎ ህይወቱን በነፍሰ ገዳዮች የተነጠቀው ማልኮም ኤክስ፤ “ጥቁሮች ከነጮች ተለይተው ለብቻቸው መኖር አለባቸው” የሚል ጥቁር ብሔርተኝነትን የሚያበረታታ ትግል አራማጅ ነበር፡፡

ሁለቱ ሰዎች ሁለት ዓይነት ህልም ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ልዩነቶቻቸውን አጥበውና አቻችለው ትግሉን ማስተባበር ችለዋል፡፡ የማርቲን ሉተር ኪንግ ታሪካዊ ንግግር ሃምሳ አምስተኛው ዓመት ሲታወስ፤ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ የታለመላቸውን ህልም እየኖሩ ነው “dreams comes true” እንዲሉ!! … 

አንድ ቀን ልጆቼ ከነጮች ዕኩዮቻቸው ጋር በአንድ ት/ቤት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ይማራሉ ብሎ ነበር፡፤ … ሆነ፡፡ … አንድ ቀን ጥቁርና ነጭ ዜጎች በአንድ አውቶብስ ውስጥ ጎን ለጎን ተቀምጠው ይጓዛሉ ብሎ ነበር፡፡ … ሆነ …፡፡ ሌሎችም ብዙ ነገሮች ሆነዋል፡፡  

… የintegration (ተደማሪነት) ፍልስፍናው ሊሰናከል ያልቻለው የሰውን ልጅ የታሪክ ዕድገት ያገናዘበ በመሆኑ እንደሆነ ተመስክሮለታል፡፡ ሰብዓዊነቱም ከእነ ጋንዲና ኔልሰን ማንዴላ ጋር የሚያዳምረው መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ታላቋ አሜሪካ ለውለታው የልደት በዓሉን በየዓመቱ በድምቀት ታከብራለች፡፡ 

ይህም በዘረኝነት ላይ የተመዘዘ ቀይ ካርድ ማረጋገጫ ሲሆን የ“DV” ሎተሪም በካርዱ ላይ እንደተፈረመ ማህተም ሊቆጠር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡  

ወዳጄ፡- መጪውን ጊዜ ያገናዘበ ህልም ወይም የፖለቲካ አመለካከት በጊዜ ሂደት ዕውን መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አንዳንድ አመለካከቶች ደግሞ ከስሜትና ከግላዊ ምኞት የመነጩ በመሆናቸው ቅዠት ሆነው ይቀራሉ፡፡ አደጋው ቅዠትነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ለተረት እንኳ የሚዘገንን ጥፋት ማድረሳቸው ነው፡፡ ይህም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፣ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ደርሶ አይተናል፡፡ እዚህም እያየን ነው፡፡  

ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ፡- ሕዝባችን ለግልም ሆነ ለማህበራዊ ዕኩልነት፣ ለአስተማማኝ ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ በጋራ እንዳይሰለፍ የዘር ፖለቲካው እንቅፋት ሆኗል፡፡ ሕዝባችን የተሸከመውን ድህነት በመተጋገዝ እንዳያራግፍ፣ አዲስ የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ መደብ ጫና በጋራ እንዳይቋቋም የዘር ፖለቲካው ጋርዶታል፡፡

የትምህርትን ደረጃና ጥቅም ዝቅ በማድረግ ታላላቅ ሳይንቲስቶች፣ አርቲስቶች፣ አርቆ አሳቢ መሪዎችና ፈልሳፊዎች ከማፍራት በተቃራኒ ወሬ በማመላለስ የሚኖሩ፣ መመሪያ አስፈፃሚዎችና ዘመናዊ የመንግስት ባሪያዎች እንዲፈለፈሉ የዘር ፖለቲካው ምክንያት ሆኗል፡፡

ዓለም ጥሏቸው የተሻገራቸውን ጎታች እምነቶችና አጉል ልማዶች “ባህል ናቸው” በማለት በመቆስቆስና በማበረታታት ህዝባችን የስልጣኔ ፀሐይ እንዳይሞቀው በማድረግ ኋላ ቀርነት ላይ እንዲቸከል አድርጎታል … የዘር ፖለቲካው!!

ወዳጄ፡- እኛ እሹሩሩ የምንለው የዘር ፖለቲካ፤ በዚህም ሆነ በዚያ ቢታሰብ የሰለጠነው ዓለም ቆርጦ የጣለው የቅዠት ነቀርሳ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በጊዜ ካልነቃህበት የነፍስህን ብርሃን ያሳውራል፡፡ … አበቦቹ ሲፈኩ፣ ከዋክብቱ ሲደንሱ፣ ወፎቹ ሲዘምሩ፣ አሶቹ ሲንቦጫረቁ፣ ህፃናቱ ሲንጫጩ፣ ቡችሎቹ ሲላፉ አይታይም፡፡ .. አውሮሃላ!!

ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- መጽሃፉ ተፅፎ ተጠናቀቀ ብለናል፡፡ ደራሲው ስሙንና የመጽሃፉን ርዕስ ለመጻፍ ብዕሩን አነሳ፡፡ … ስሙና ማስታወስ አልቻለም። ቢያስብ፣ ቢያስብ… አልሆነም፡፡ 

መታወቂያውን ለማየት ኪሱን ቢዳብስ የለበሰው ፒጃማ ነው፡፡ ወደ መኝታ ቤቱ ሄደ፡፡ ከኮቱ ውስጥ መታወቂያውን አውጥቶ ስሙን ሲያነብና ፎቶ ግራፉን ሲመለከት ከእንቅልፉ ባነነ፡፡ … 

ለዓመታት ግራ ሲጋባበት የቆየበትን ጉዳይ አወቀ። በማግሥቱ ወደ ስራው ሲሄድ መጽሃፉን ገለጠና እንዲህ ፃፈ፡-
ርዕስ፡- ህልሙን የኖረ ሰው
ደራሲ፡- እኔ 

ሠላም!!

ምንጭ - አዲስ አድማስ
 

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply