የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠንና ኢንቨስትመንትን እንዲሁም የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ያለውን ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍ እና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት የኢንቨስትመንት መስክ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያላለፈ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብረው መስራት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሎጂስቲክስ እና የጉምሩክ አሰራሮችን ማሻሻል እንደሚገባ ታምኖ ውሳኔው ሲጠበቅ እንደነበረ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዛሬ ባወጠው መግለጫ አመልክቷል።
ጨምሮም ዘርፉ ካሉበት ውስንነቶች መካከል የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ በመገደቡ በውጪ ንግድ ምርት የሥራ ዘርፍ እና በሌሎች የገቢና ወጭ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸው ጠቅሷል።
በተለይ ዓለም አቀፍ አምራች ድርጅቶች በሌሎች ተወዳዳሪ በሆኑ ሃገራት በቀላሉ የሚጠቀሙባቸውን አገልግሎቶች በሃገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸውን እየጎዳው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲገልፁ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ተኮር በሆነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተለዋዋጭ ከሆነው የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ ጋር አብራ እንድትጓዝ ለማድረግና ዘርፉ ለሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎችና እራሱን ችሎ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያበረክትበትን አሰራር ለመዘርጋት እንዲያስችል ማሻሻያ መደረጉ ተገልጿል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብሮ መስራት የሚያስችላቸውን ማሻሻያዎች በማድረግ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማስጠበቅ፣ ብሎም የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማስቻል የውጭ ባለሃብቶች አናሳ ድርሻ በሚይዙበት መልኩ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉ ተገልጿል።
የኢንቨስትመንት ቦርዱም በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልሎ የነበረውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍ እና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት የኢንቨስትመንት መስክ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከግማሽ በታች ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብረው መስራት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል።
No comments: