Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

አዲሱን ዓመት ስንቀበል የተሻለች ጠንካራ አገር ለመፍጠር ያሳየነውን ተነሳሽነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሊሆን ይገባል! “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር“ በሚል መሪ መልዕክት መላው ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ለመቀበል እየተሰናዳን እንገኛለን። 


እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሰን! መጪው ዘመንም የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የዕድገት እና የብልጽግና እንዲሆንልን የኢፌዴሪ መንግሥት መልካም ምኞቱን ከወዲሁ ይገልጻል።

የኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑ የተመሰከረለትን የወርሃ ጳጉሜን አምስት ቀናት የሰላም ቀን፣ የፍቅር ቀን፣ የይቅርታ ቀን፣ የመደመር ቀንና የአንድነት ቀን በሚል በነባር ኢትዮጵያውያን እሴቶች ቅኝት ዋዜማውን እያከበርን እንገኛለን።

ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ተኳርፈው እና ተራርቀው የነበሩ የአንድ እናት ልጆች፣ ጎራ ለይተው ሲቆራቆሱ የነበሩ የኃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅቶች ከጥላቻ ተላቀው በፍቅር እና በመደመር እሳቤ በአንድ ማዕድ ዙሪያ በገዛ አገራቸው በተሰባሰቡበት ሁኔታ የበዓሉ ዝግጅትም ይሁን በተለያዩ አገራዊ እሴቶች ተቃኝቶ በመካሄድ ላይ ያለው የዋዜማ አከባበር እየተካሄደ መሆኑ በዓሉን የተለየ ያደርገዋል።

በተጨማሪም በደምና በታሪክ ከተሳሰረው የኤርትራ ወንድም ህዝብ ጋር ለዓመታት የዘለቀው የጥላቻ እና የጦርነት አስተሳሰብ ተወግዶ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እየሰሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ተወካዮቻቸው የሚታደሙበት በዓል መሆኑም ሌላው መለያው ነው።

ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ምንጭና የነፃነት ጮራ ፈንጣቂ መሆኗን ከሚመሰክሩላት በርካታ ቋሚ ቅርሶች መካከል አንዱ የራሷ ልዩ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት መሆኗ ነው። ከዘመን መቁጠሪያዋ የሚመነጨው የዘመን መለወጫ በዓልም በኢትዮጵያውያን ወግና ባህል መሠረት በየዓመቱ አዲስ ተስፋና ምኞት ይዞ የሚመጣ ታላቅ በዓል ነው።

በተለይም ላለፉት ጥቂት ወራት በአገራችን በተጀመረው የለውጥ ነፋስ ታጅቦ፣ በአዲስ የለውጥ ተስፋ እና ብርሃን ተሞልቶ ብቅ ያለው የዘንድሮው በዓል ከቀደሙት በዓላት ጋር ሲነጻጸር ፍጹም የተለየ ክብደት እንዲሰጠው ያደርገዋል። 

የዘንድሮውን በዓል የተለየ እንዲሆን ካደረጉት ጉዳዮች መካከልም በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ የጥላቻው ግንብ ፈርሶ በምትኩ የፍቅር ድልድይ እየተገነባ ባለበት ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑ ነው። ለውጡን ተከትሎ የተመዘገቡ ሌሎች በርካታ እና ትላልቅ ድሎች መኖራቸውም በብዙ መልኩ የተለየ ያደርገዋል።

ከተጀመረ በጣም አጭር ሊባል በሚችል ጊዜ ውስጥ በመንግሥት የተካሄዱት የለውጥ እርምጃዎች ከአገራችን አልፎ የምንገኝበትን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገራትን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ናቸው። 

“የእኛ ሰላም እና እድገት የምስራቅ አፍሪካ አገሮችም ሰላም እና እድገት ነው” በሚል የላቀ እሳቤ ላይ ተመስርቶ መንግሥታችን ያራመደው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባር እየተሸጋገረ በውጤት እየታጀበ መምጣቱን በጂቡቲ፣ በሶማሊ እና በአሰብ ወደብ አጠቃቀም ዙሪያ የተገኘውን ውጤት እንደ አብነት ወስዶ መመልከት በቂ ነው።

በሌላ በኩል፣ ህዝባችን በትልቅ አገራዊ መነቃቃት መንፈስ ውስጥ ሆኖ እያስመዘገባቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንደ አገር የሚያኮሩን ሆነው መታየት ጀምረዋል። ነባሮቹን የሰላም ወዳድነት፣ የመፈቃቀር፣ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴቶቻችንን እንድናጎለብት በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በሙሉ ልብ በመቀበል ህዝባችን በየአካባቢው እያካሄደው ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዛሬ ከመቼውም የተሻለች ሰላማዊ አገር እንድትኖረን አስችሏል።  

“ለእናት አገሬ ስጦታ” በሚል መርህም በእውነተኛ የወገን ፍቅር ላይ የተመሰረተ እና ለአገራችን እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸውን የበጎ አድራጎት ሥራዎች በማካሄድ ላይ መሆኑን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

መላው ህዝባችን በጋራ እና በተናጠል ለአገራችን እና ለወገናችን እያበረከተ ያለው ዘርፈ-ብዙ አስተዋጽኦ እንደ አገር እጅግ የሚያኮራ እና ለወደፊት ራዕያችን መሳካትም ትልቅ ስንቅ ሆኖ የሚወሰድ ነው።  

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንደ አንድ ማሳያ ገጽታ፣ እንዲሁም በለውጡ ሳቢያ እየተመዘገቡ ካሉት ስኬቶች እንደ አንድ ስኬት ማሳያ ተደርጎ ለሚወሰደው ለዚህ መሰሉ የህዝባችን አገር ወዳድ ጥረት መንግሥት አድናቆቱን ይገልጻል፤ ምሥጋናውንም ያቀርባል።

ኢትዮጵያውያን መጪውን አዲስ ዓመት ለመቀበል ሲዘጋጁ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ የፈጠሩትን አገራዊ መግባባት አጠናክረው በመቀጠልው የጋራ ራዕይ እና ተልዕኮ አንግበው ለአገር ግንባታ የጀመሩትን ጥረት ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል። 

እያሳዩት ያለውን ከእኔነት ይልቅ የእኛነት አስተሳሰብ ጎልቶ እንዲቀጥልም ማድረግ ይገባል። በአጠቃላይ የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችውን ጠንካራ አገር ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት መላው ህዝባችን ሰላሙን በመጠበቅ እና አንድነቱን በማጠናከር አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply