Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? “የጋራ አብሮነት ውጤት ነው!” በምን ይገለፃል? “በአደዋ!”

ይህ ፅሁፍ “ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? በምን ይገለፃል?” በሚል ከአዲስ አዳምስ ለቀረበልኝ ጥያቄ የሰጠሁት ምላሽ ነው፡፡


ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው፡፡ ዜግነት ደግሞ በአንድ የተወሰነ ሀገር ውስጥ የጋራ አብሮነትን የሚያሳይ ነው፡፡ አንድ ጆሴ ኦርቴጋ የሚባል ፖርቹጋላዊ ፀሐፊ አለ፡፡ ይህ ጸሐፊ፤ ሀገር የሚመሰረተው በምን ላይ ነው? ሲል ይጠይቃል፡፡ ሀገር የሚመሰረተው በእሱ አተያይ፣ በጋራ አብሮነት (common future) ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም የጋራ አብሮነት ውጤት ነው፡፡ የጋራ መሰረት ያለን፣ የጋራ ጉዳይ ያለን፣ ለወደፊትም የጋራ እድል ያለን ሰዎች ነን፤ በኢትዮጵያዊነት ስር ነው የተሰባሰብነው፡፡፡ ይሄ ማለት ዛሬ እና ትናንት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ነገና ለወደፊትም አብሮ ለመኖር የጋራ ስምምነት ያለን ህዝቦች ነን፡፡

የአሁኗ ኢትዮጵያ እንዴት ተመሰረተች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ የአሁኗ የቆመችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው፡፡ አሁን ላይ ላለው የአንድነት ክፍፍልና የእርስ በእርስ መጠላለፍ መሰረት የሆነውም ያንን የኢትዮጵያ አመሰራረት የምንረዳበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ነው፡፡ ግማሹ በቅኝ ግዛት (ወረራ) አይነት የተፈጠረች ነች ይላል፤ ግማሹ ደግሞ ቀድሞ የነበረችውና ኋላ ላይ በታሪክ አጋጣሚ የተበታተነች ኢትዮጵያን መልሶ አንድነቷን ማስጠበቅ ነው ይላል። በዚህ መሃል ግን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች፣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ መስፋፋት ሲጀምሩ፣ በወቅቱ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግሬ በተባሉት አምስት ግዛቶች ላይ ብቻ ተወስና የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ሀገራዊ ኃይልና አንድነት ለማጠናከር፣ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ መስፋፋት ጀመረች፡፡

አፄ ምኒልክ፤ በሉአላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት፣ ሁሉም በጋራ መቆም አለባቸው ከሚል መነሻ ነው መስፋፋትን ያደረጉት፡፡ በዚህ መሃል ግጭት ተፈጥሮ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ይሄ ክስተት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ሆኖ የሚታየው አብዛኛው ሀገር፣ አሁን ላይ የያዘው ቅርፅ በእንዲህ አይነት ክስተቶች አልፎ የመጣ ነው፡፡ የዚህ አይነት የማሰባሰብ ውጤት የታየው በአድዋ ጦርነት ላይ ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በግልፅ ለአንዲት የጋራ ሉአላዊ ሀገር ተዋድቀዋል፡፡ ስለዚህ አድዋ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ነው፡፡ አድዋ ላይ የምናየው ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጋራ የሉአላዊነት አደጋን የቀለበሱበትና አብሮነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ወደፊትም በነፃነት ለመኖር የተስማሙበትና መስዋዕትነት የከፈሉበት፣ ሁሉም ለወደፊት አብሮነታቸው አሻራቸውን ያሳረፉበት ነው አድዋ ማለት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ለኔ አድዋ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት በአብሮነት፣የወደፊት ነፃነትን አስከብሮ፣ በጋራ ለማደግ የመስማማት ውጤት ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ነው ነፃነታችንን አስከብረን ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ቅኝ ግዛት ውስጥ የወደቁበት ሚስጥሩ፣ ይሄን አብሮነት ማጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆንነውና ራሳችንን አስከብረን የኖርነው፡፡

የኢትዮጵያ አንድነትን ለማምጣት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ብዙ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡ ይሄ ግን እኛ ብቻ ሳንሆን ሰልጥነዋል የተባሉ ሀገሮችም የዛሬ አንድነታቸውን ያገኙት፣ በእንዲህ ያለውና ከዚህም በከፋ ሂደት ነው፡፡ አኖሌ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ፣ የኢትዮጵያ አንድነት በሚመሰረትበት ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ነው፡፡ አኖሌ ላይ ወገኖቻቸው የተጨፈጨፉባቸው ሰዎች ናቸው፣ አድዋ ላይ ለጋራ ነፃነት የተዋጉት፡፡ አድዋን ያለ ኦሮሞ ብሔር ተሳትፎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የአፄ ምኒልክ ወታደር ኦሮሞ ነው፡፡

አሁን የሚንጸባረቀው የመበደል ስሜትና የብሔርተኝነት ስሜትም ሂደት የፈጠረው ነው። በየትኛውም ተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ባለፈ ሀገር ይሄ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይን ማንሳት እንችላለን፡፡ ይሄ የመበደል (ብሔርተኝት) ስሜትና የአንድነት ስሜትን የማራመድ ጉዳይ አዲስ ክስተት ሳይሆን ሊፈጠር የሚችል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ልሂቃን እንደሚሉት፤የሀገር አብሮነትን ለማስጠበቅ፣ ይሄን አይነቱን የበደለኝነት ስሜት መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ አሰቃቂ ክስተቶችን መዘንጋትና አስተማሪ ወይም በጎ የሆኑትን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ሀገር ያለው የብሔርተኝነት ስሜት መሰረቱ የበደለኝነት ስሜት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት ጎራ ደግሞ የግድ ኢትዮጵያዊ አንድነትን መቀበል አለብን ብሎ መጫን አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከእንግዲህ ወዲህ፣ ፈቅደን መርጠን የምንወስደው እንጂ በግድ የሚጫንብን መሆን እንደሌለበት ማስተዋል አለብን።

የብሔርተኝነቱና የአንድነቱ ጎራ ግጭት በዚህ መንገድ መታረቅና የጋራ የወደፊት አብሮነት መታሰብ ይኖርበታል። የበደለኝነት ስሜትን ትቶ አንድነትን ለማሰብ የአኖሌን ጭፍጨፋ ዘወትር ማንሳቱን ትተን፣ አንድ ያደረገንን አድዋን መዘከር አለብን፡፡ በጎ የታሪክ ገፅታችንን ማጉላት ይገባናል። የቀድሞ ታሪካችን ላይ ቆዝመን አንድነታችንን መሸርሸር ትተን፣ በወደፊት አብሮነታችንና የጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተ የጋራ አንድነትን ለመፍጠር መጣር አለብን፡፡ የፖለቲካ ሃይሎችም አቅጣጫቸው፣በወደፊት የጋራ አብሮነት ላይ የሚያጠነጥን መሆን አለበት፡፡ አሁን ልዩነቶችን ማጉላት ላይ ነው ያተኮርነው፡፡

ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ትግሬ እያልን እርስ በእርስ የምንከራከረው፣ የጋራ ጉዳይ፣ የጋራ አገር ስላለን ነው፡፡ ክርክሩ ራሱ የተመሰረተው በጋራ ጉዳያችን ላይ ነው፡፡ አሁን ማተኮር ያለብን “ለወደፊት በጋራ እንዴት እንኑር” በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እየከረረ የመጣውን ልዩነታችንን ማስታረቅ እንችላለን፡፡

ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

ከእኔ ጋራ ሌሎች ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ዶ/ር ንጋት አሰፋ፣ ያሬድ ሹመቴ እና ዳንኤል ብርሃኔ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ሙሉ ዘገባውን ይህን ማስፈንጠሪያ (Link) በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ!

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply