የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሰት “በሽብርተኝነት” “የአገርን ሰላም በማደፍረስ” “ህገ መንግስታዊዉን ስርአት በመናድ ” “በዘር ማጥፋት” “በአገር መክዳት” ወዘተ… የሚሉት የወንጀል ክሶች አላማ ግልፅ በመሆኑ ዜጎች በመንግስት ላይ ምንም እምነት የላቸዉም። በመንግስትና በሚወነጅላቸዉ መካከል ያለዉን ግንኙነት ጠንቅቆ ያዉቃልና….የፍርድ ቤት ዉጣ ዉረዱ፤ የሰዉ ሃይል፤ የቁሳቁስና የጊዜ ብክነት ለምን እንዳስፈለገ የሚጠይቁም አልጠፉም። የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎቹን በማይቀበሉትና በሚተቹት ላይ መንግሰት በየጊዜዉ የሚወስደዉ ይህ እርምጃ ህግን የተንተራሰ ነዉ በሚል ግምት ለማታለልና ለማሳመን ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄያችን “ማንን?” የሚል ነዉ። ተከሳሾችን? መንግስት እራሱን? ህዝብን? ወይንስ አለምአቀፉን ህብረሰብ?
በተለይም እኤአ በ2009 የወጣዉ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ህግ “የመንግስት ጠላቶች” በሚላቸዉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፤ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች፤ ጋዜጠኞች እና በህወሃት/ኢህአዴግ ላይ ጠንከር ያለ ሂስና ትችት በሚሰነዝሩ ዜጎች ላይ እርምጃ ለመዉሰድ፤ ህዝብን በፍርሃት ለማሸማቀቅ ያነጣጠረ መሆኑን ብዙዎች ይረዳሉ።
በመሆኑም መንግስት “ሽብር ፈጣሪ” ወይንም “የሽብር ተግባር” ሲል ምን ማለቱ ነዉ? በማለት ግራ ይጋባሉ። “የሽብር ተግባር” ምንድነዉ? ማነዉ ምን እየፈፀመ ያለዉ? በማለት ይጠይቃሉ።
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ከ”ሽብር” ትርጉምና “የሽብር ተግባር” በመነሳት ባለፉት 20 አመታት ማን፤ በማን ላይ ምን፤ለምን፤ ፈፀመ? ብለን አንኳር የሆኑትን መለስ ብለን መፈተሽ ይገባናል።
ለግንዛቤ እንዲረዳ በሽብርተኝነት ላይ የተሰጡ ትንታኔዎችን መሰረት በማድረግ አለም አቀፉ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት ያጠናቀራቸዉን አመታዊ ሪፖርቶች ማገላበጥ የግድ ይሆናል።
ሽብርተኝነትና የሽብር ተግባር

ሽብርተኝነት በታሪክ ረዢም ጊዜ ያስቆጠረ ነገር ግን፤በአንፃሩ ትክክለኛ ትርጉም ያልተገኘለት ነዉ። በአንድ በኩል ወንጀል ነዉ፤ በሌላ በኩል ለአላማ የሚፈፀም ተግባር ነዉ። ለአንድ ወገን ጭቆናን ለመታገል መፈፀም ያለበት፤ተቀባይነት የሚኖረዉ አማራጭ ድርጊት ነዉ። ለሌላዉ ወገን ስንኳንስ ሊፈፀም ሊታሰብ የማይገባዉ፤ ይቅር የማይባል የጭካኔ እርምጃ ነዉ።
የሽብርተኝነት ትርጉም ለተፈፀመዉ ድርጊት ከሚሰጠዉ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተሳሰብና ለፈፃሚዉ ከሚኖር ግምት ይመነጫል። ይሁን እንጂ የሽብር ተግባር ከሁለት ተፋላሚ ሃይሎች የቆመለትን አላማ በተለያየ ምክንያት የማስፈፀም ድክመት ባለዉ በአንዱ የሚወሰድ የማጥቃት አማራጭ ዘዴ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ለሽብርተኝነት የሰጠዉ ትርጉም፤
“የፖለቲካ፤ የሃይማኖት ወይንም የፍልስፍና አላማን ለማራመድ በመንግስት ወይንም በህብረተሰብ ላይ ሆን ተብሎ ታስቦበት የሚፈፀም ህገወጥ የአመፅ ተግባር፡ ወይንም ማስፈራራት ነዉ”
የአሜሪካን የፌዴራል ምርመራ ቢሮ /ኤፍ ቢ አይ/ በበኩሉ፡” ሽብርተኝነት ፖለቲካዊ ወይንም ማህበራዊ አላማዎችን ለማራመድ ህገወጥ የሆነ ሃይልና አመፅን በመጠቀም በመንግስት፡ በሰላማዊ ህዝብ ወይንም በአንድ የተወሰነ ክፍል ላይ ጫና ለመፍጠር በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስና ማስፈራራት ነዉ።” በማለት ይተረጉመዋል።
የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሌላ በኩል፤” ሽብርተኝነት ከፖለቲካዊ ፍላጎት የሚመነጭና የታሰበበት፤ ተሰሚነት ወይንም ተደማጭነት ለማግኘት ተፋላሚ በማይሆኑ ኢላማዎች ላይ የሚያነጣጥር፤ የህብረተሰቡ አካል በሆኑ ቡድኖች ወይንም በህቡዕ በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የሚፈፀም የጥቃት እርምጃ ነዉ።” በማለት ይገልፀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ በ1992፤ ለሽብርተኝነት የሰጠዉ ትርጉም ቢኖርም አላማ፤ ድርጊትና አፈፃፀሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዉስብስብ እየሆነ በመሄዱ ሌላ ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት በመስራት ላይ እንደነበር ይታወቃል።
ዞሮ ዞሮ ሽብርተኝነት ከድርጊቱ ሰለባዎች ባሻገር በአካባቢ በነበረዉ ተመልካች፤ በሕዝብ፤ በመንግስት እና በአለም አቀፉ ህብረተሰብ ትኩረት ለማግኘት የሚፈፀም ጥቃት ነዉ።
በአለማችን በርካታ የሽብር ተግባራት ተፈፅመዋል። በ1972 በሙኒክ ኦሎምፒክ ወቅት ብላክ ሰፕቴምበር በተባለዉ ቡድን በእስራኤል ስፖርተኞች ላይ የተፈፀመዉ፤ በቤይሩት አለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ በአሜሪካ የባህር ሃይል ባታሊዮን ምድብ ወታደራዊ አባላት ላይ፤ በሰፕቴምበር 11/2001 በአሜሪካ የንግድ ማዕከል ሁለት መንትያ ህንፃዎች ላይ፡በናይሮቢ፤በለንደን፤ በስፔን፡ በህንድ፤ በአፍጋኒስታን፤ በኢራቅና በሌሎችም ስፍራዎች የተፈፀሙት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸዉ።
ለአንዱ እንደ “ሽብር ፈጣሪ” ተደርጎ የሚቆጠር ፈፃሚ፤ ድርጊቱን ለሚደግፍ ሌላ አካል እንደ “ነፃነት ተዋጊ” ሊቆጠር ይችላል። የሽብር ድርጊት ፈፃሚዎች እራሳቸዉን ወንጀለኛ አድርገዉ አይቆጥሩትም፤ይልቁንም ላመኑበት አላማ የፈፀሙት “ትክክለኛ” ተግባር አድርገዉ እንጂ። ይሁንና ጉዳት የደረሰበትና በደረሰዉ አስከፊ ጉዳት ሀዘን የተሰማዉ ወገን ለሰዉ ሕይወት ርህራሄ የሌላቸዉ ወንጀለኛ አድርጎ እንደሚመለከታቸዉ ግን ግልፅ ነዉ።
ሕዝብ በግልፅ የጥቃቱ አላማ ደጋፊና የጥቃቱ ጉዳት የሀዘን ተካፋይ በመሆን አቋም ሊይዝ ይችላል። በመሆኑም አንድ የተፈፀመ የሽብር ተግባር በህዝብ ዉስጥ የሚያሳድረዉን ስሜት በቀጥታ መገመት አስቸጋሪ ነዉ። በህብረተሰቡ ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገፅታ፡ የሽብሩ የጉዳት መጠንና የፈፃሚዉ አላማና ማንነት ህዝብ በግልፅም ሆነ በስዉር የሚወስደዉን አቋምና የሚያድርበትን ስሜት ይወስኑታል።
በ1790ዎቹ የፈረንሳይ አብዮታዊ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በመግደልና በመጨቆን ለመግዛት ሽብርተኝነትን በመሳሪያነት ተጠቅሞበታል። ድርጊቱን ግን ህብረተሰቡ አልተገነዘበዉም ማለት አይቻልም።
ባለንበት አለም ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ለሽብር ተግባሮች መፈፀም ምክንያት ናቸዉ።ግራ ዘመም የሆኑ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አብዮታዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦች፤ወይንም ቀኝ ዘመም የሆኑ ብሄርተኝነትና ጠባብ ጎሰኝነት የመሳሰሉት የቡድን ፍላጎቶች በየደረጃዉ በሃይል ሲታገዙና አምባገነናዊ ቅርፅ ሲይዙ ለሽብር ተግባር ምክንያት ይሆናሉ።
በሌላ በኩል ፅንፈኛ የሆኑ የሃይማኖት ተከታዮች መንግስታት የሚያወጧቸዉ ህጎችና መመሪያዎች በግል ሃይማኖታቸዉ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚል እምነት ሲያድርባቸዉና በሌላም በኩል ከሌላዉ ሃይማኖት በላቀ ለግል ሃይማኖታቸዉ ግምት መስጠት ሲጀምሩ የሽብር ተግባር ይፀነሳል።
መንግስታትና መሪዎች ግላዊም ሆነ ድርጅታዊ አላማዎቻቸዉን በሃይል ተግባራዊ ለማድረግ እብሪት ሲያድርባቸዉ ተቀናቃኞቻቸዉንና ህዝባቸዉን ማሸበርን አማራጭ አድርገዉ ይወስዱታል። መንግስታዊ የሽብር ተግባሮች እጅግ አሳሳቢ ናቸዉ። የመንግስት ተቋማት በየደረጃዉ የሽብር ማስፈፀሚያ መሳሪያ በሚሆኑበት ህብረተሰብ ዉስጥ ሕግጋት፤ዜግነት፤ሉዓላዊነት፤ልማትና ሰላም የሚባሉት ፅንሰ ሃሳቦች ትርጉም አይኖራቸዉም። አገራዊ ራዕይ ይጠፋል፤ በምትኩ ስርኣተ አልበኝነት ይነግሳል።
መንግስታት የሚፈፅሟቸዉ የሽብር ተግባራት በ3 መንገዶች ይተገበራሉ።
ሀ/ ቀጥታ ሽብር በመፈፀም፡
ይህ በቀጥታ እንደፖሊሲ ታምኖበት በመንግስት የሚፈፀም ነዉ። የፍትህ አካላቱ ፍርድ ቤት፤ አቃቤ ህግ፤ ወህኒ ቤት፤ ፖሊስ፤ የወታደሩ ክፍልና ሌሎችም የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማትን በመጠቀም ተግባራዊ የሚደረግ ነዉ። ለመንግሰት ዓላማ ሊዉሉ የሚችሉ አዳዲስ ህጎችን እንዳስፈላጊታቸዉ በማዉጣት፤ያሉትን በማሻሻል፤በማጠናከር፤ በመለወጥና ተዛማጅ ትርጓሜ በመስጠት ይተገበራሉ።
በዜጎች ላይ ሰቆቃ፤ ድብደባ ማሰቃየትና ግድያ በመፈፀም፤ በየደረጃዉ በተዋረድ እንዲፈፀም በመፍቀድ፤ ሰራተኛዉን ከስራ ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም በማገድ፡ የጡረታና ሌሎች የማህበራዊ መብቶችን በመንፈግ፤ ፖሊሲን በማስፈፀም ስም ከንብረት ባለቤትነት በመንቀል፤ ከይዞታ በማፈናቀልና ተመጣጣኝ ባልሆነ ካሳና ምትክ መንጠቅ ሊጠቀሱ ከሚችሉ የቀጥታ መንግስታዊ ሽብር ስልቶች ጥቂቶቹ ናቸዉ።
በጀርመን ናዚዎች ስልጣን እንደጨበጡ በግልፅ የተከተሉት ፖሊሲ “የመንግስት ጠላቶች” ባሏቸዉ ላይ ሆን ብለዉ የወሰዱት የማጥፋት ዘመቻና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በህዝብ ላይ ፍርሃትና ጭንቀት መፍጠር እንደሆነ ይታወሳል።
በተመሳሳይ መንገድ እኤአ በ1930 ስታሊን የጀመረዉ “ማፅዳት” የተሰኘዉ ፖሊሲ የመንግሰትን ተቋሞች በመጠቀም ዜጎችን ለማሸበር የተጠቀመበት ዘዴ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ዘዴ በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚፈፀሙት የሃሰት ክሶች፤ መንግስቱ በጠላትነት በሚቆጥራቸዉ ቤተሰቦች፡ ጓደኞች፡ ዘመዶችና፡ ግንኙነት አላቸዉ ብሎ በሚጠረጥራቸዉ ላይ የሚደርሰዉ ማስጠንቀቂያ፤ ቅጣት፤ እስራት፤ እንግልትና ጉዳት ይጠቀሳሉ። ለፖሊስ፤ ለደህንነትና ለወታደራዊ ክፍሎች እንዲሁም በየእርከኑ ለሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ከህግ ዉጭ የሚሰጠዉ ስልጣንና ሃላፊነት የመንግስታት የቀጥታ ሽብር መገልገያ መሳሪያ ናቸዉ።
ለ/ በሽብር ተግባር ዉስጥ ተሳታፊ በመሆን
መንግስታት ለአገዛዛቸዉ “አደገኛ” ናቸዉ ብለዉ በሚገምቷቸዉ የራሳቸዉ የህብረተሰብ ክፍል/ህዝብ፤ቡድኖችና ግለሰቦች ወይንም ሌሎች መንግስታት ጥቅምና ፍላጎት ላይ፤ ግልፅ ባልሆነ መንገድ የፀጥታ ሰራተኞቻቸዉ በማሰማራት የሚያስፈፅሙትና ከበስተጀርባ በመሆን ተሳታፊ የሚሆኑበት የሽብር ተግባር ነዉ።
ነፍሰ ገዳዮችን እስከ ዉጭ አገር ድረስ በማሰማራት “አደገኛ” ብለዉ በጠላትነት የፈረጇቸዉን የኮበለሉ ዜጎች ማፈን፤ ከተቻለ መግደል፤ የወንጀል ወጥመድ አዘጋጅቶ በእጅ አዙር ማስያዝ፡ ስም ማጥፋት የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ናቸዉ።
ምንጫቸዉ ባልታወቁ መረጃዎች በአንድ አካባቢ ጥርጣሬና አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ፤ ሁኔታዎችን በስዉር ማመቻቸት፤ቅራኔዎች ወይንም ግጭቶች እንዲከሰቱ ማድረግ፤ ከተቻለ በግጭቱ ጣልቃ የፀጥታ አስከባሪ ወይንም ቅጥር ሃይሎችን አስርጎ ማስገባት፤ ሁኔታዎችን ማባባስ፤ በእጅ አዙር ህገ ወጥ እርምጃዎችን መዉሰድ፤ እንደመንግስት ችግሮቹን ለማስወገድ በወቅቱ በስፍራዉ አለመድረስ፡ በግልግልና በአስማሚነት አሊያም በዉሳኔ ሰጪነት የሆኑ የመንግስትን ስዉር ፍላጎት ሊያስፈፅሙ የሚችሉ አሻሚ ዉሳኔዎችና እርምጃዎችን መዉሰድ የመንግስት የሽብር ተሳትፎ ስልቶች ናቸዉ።
ሐ/ ሽብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሃይሎችን ስፖንሰር አድርጎ በማሰማራት
መንግሰት ስፖንሰር የሚያደርጓቸዉና የሚደግፏቸዉ እነዚህ ተግባራት መንግስታት አስፈላጊ መሳሪያ፤ ስልጠና እና ሌሎችንም ድጋፎች በመስጠት በሚያቋቁሟቸዉና፤ በሚያሰማሯቸዉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚፈፀሙ ናቸዉ።
የድርጊቱ ፈፃሚዎች ደህንት እንዲጠበቅ በቀላሉ የማይደፈር ስፍራና አካባቢ ይኖራቸዋል። የሃሰት ሰነድ በስማቸዉ ይዘጋጅላቸዋል፤ ተሽከርካሪና ያልተመዘገበ የሰሌዳ ቁጥር፤ የመታወቂያ ወረቀት፤ፓስፖርት፤ ለባንክ ሂሳብና ለፋይናንስ እንቅስቃሴ የሚረዱ የንብረትና የንግድ ባለቤትነት የፈቃድ ወረቀቶች፤ የጦር መሳሪያ የመያዝና የመግዛት ፈቃድን ጨምሮ ካስፈለገ ከአንድ በላይ በተለያየ ስም ይዘጋጅላቸዋል።
በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገር ለሽብር ተግባሩ ስኬት በትምህርት ወይንም በስልጠና ላይ እንዲቆዩ ከፍተኛ ወጪ ይመደባል። እንዳይያዙ የሚረዳ በዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ ይሰጣቸዋል፤ በኤምባሲ ቅጥር ግቢ ሊገለገሉ እንዲችሉ ይፈቀድላቸዋል፤ ከኤምባሲ ወይንም ከባንክ ሂሳብ ወይንም ሀዋላ የሚቀበሉት ገንዘብ ይመደብላቸዋል፤ በበረራ ወቅት የዲፕሎማቲክ ከረጢቶችን በመጠቀም የጦር መሳሪያና የመገናኛ መሳሪያዎች ያለችግር ለመጓጓዝ እንዲችሉ ይደረጋል። ተደርሶባቸዉ ተይዘዉ ከተሰጡት ወይንም ከድርጊቱ መፈፀም በሁዋላ እንደሁኔታዉ ጠብቆ ያሰማራቸዉ መንግስት እራሱ ሊያጠፋቸዉ ይችላል።
አምባገነን መንግስታትና “ሽብርተኝነትን መዋጋት”
በአሁኑ ወቅት አምባገነን መንግስታት የፖለቲካ ፕሮግራማቸዉን የሚቃወሙና የማይቀበሉ ግለሰቦችን፤ ቡድኖችንና ድርጅቶችን ለማጥቃት “ሽብርተኝነትን መዋጋት” የሚለዉን ሽፋን በስፋት እየተጠቀሙበት እንደሆነ አለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት /ሂዩማን ራይትስ ዎች / አስታዉቋል።
በማእከላዊ እስያ ቻይና፤ ሩሲያ፤ ካዛክስታን፤ ኪርጊስታን፡ ታጃክስታንና ኡዝቤክስታን በአባልነት የሚገኙበት የሻንጋይ የትብብር ቡድን “ሽብርተኝነት” በ”መዋጋት” ስም በጠላትነት በሚመለከቷቸዉ የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ላይ ጭካኔ የተመላበት እርምጃ በመዉሰድ ላይ እንዳሉ የድርጅቱ ሪፖርቶች ያስረዳሉ።
አለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት /ሂዩማን ራይትስ ዎች / ይህን የጭካኔ ድርጊት የሚፈፅሙት አምባገነን መንግስታት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባና ዩናይትድ ስቴትስ እና የምእራብ ተባባሪዎቹ “ሽብርተኝነት”ን በ”መዋጋት” አጋር አድርገዉ የሚቆጥሯቸዉ መንግስታት የሚፈፅሙትን ይህን መሰል ወንጀል አይተዉ እንዳላዩ መሆናቸዉ ከተጠያቂነት እንደማያድናቸዉ አስጠንቅቋል።
ሽብርን በዜጎችና በተቃዋሚ ሃይሎች ላይ ጥቃት የመፈፀሚያ መሳሪያ በማድረግ በሚያገኙት “ድል” በየደረጃዉ ስርኣተ አልበኝነት ሲሰፍን መንግስታቱ ብቻ ሳይሆኑ ለመንግስታቱ የቀረቡ ግለሰቦችና ተቋማት ሁሉ በአሸባሪነት እራሳቸዉን ከህግ በላይ ማኖር ይጀምራሉ።የዚህ ድምር ዉጤት ደግሞ አገራዊ ዉድቀት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይላቀቁት አገራዊ ነቀርሳና ንቅዘትን ያስከትላል።
የሕወሃት/ኢህአዴግ መንግሰት በኢትዮጵያ ዉስጥ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ነፃ ጋዜጠኞች፤ የሲቪክ ማህበራትና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም አፍቃሬ አንድነት ወገኖች ላይ በፀረ-ሽብር አዋጁ በመጠቀም በመፈፀም ላይ ያለዉ ተግባር ከዚህ የተለየ አይደለም። አገሪቱን በየደረጃዉ ስርኣተ አልባ አድርጎ ሸርሽሮ ለዉድቀትና ለዉድመት ከመዳረግ ባሻገር የማትላቀቀዉ አገራዊ ነቀርሳ ወደ መሆን በመሸጋገር ላይ እንዳለ መተንበይ ነቢይነትን አያሻም።
ወደ መንግሰት ስልጣን ከመምጣቱ በፊት “ነፃ አዉጪ” ተብሎ በሚጠራበት ወቅት በመንግሰት ተቋማትና የመሰረተ ልማት አዉታሮች ላይ ሲፈፅም የነበረዉን እናስታዉሳለን። አመራሩን በተቃወሙ በራሱ አባላትና ቀዳማይ የወያኔና የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲን /ኢህአፓ/ በመሳሰሉ ድርጅቶች ላይ ይፈፅማቸዉ የነበሩትን ተግባራት የኢትዮጵያ ህዝብ አይዘነጋቸዉም። ከሁሉም በላይ እኤአ በ1984 በረሃብተኛ ወገኑ ስም የተለመነዉን ገንዘብ ለድርጅቱ ማዋሉና የራሱን ህዝብ ሃዉዜን ገበያ ሜዳ በደርግ የጦር አዉሮፕላን ቦምብ ማስደብደቡ ለማንነቱ ማስረጃ ናቸዉ።
የዚያን ወቅቱን ህወሃት/ኢህአዴግ ማንነት ከዛሬዉ ማንነቱ ለይተን መመልከት የሚገባን መሆኑ ግን አያከራክርም። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ እንደ መንግሰት እንዳንመለከተዉ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ባለፉት ሃያ አመታት በተለይም ፖሊሲዎቹን በሚቃወሙት ላይ በተደጋጋሚ የሚፈፅማቸዉ ተግባራት “ለጊዜዉ የሚፈጥሩት ተዓምር የለም፤” በሚል “ትዕቢትና ዕብጠት” በመወጠሩ እንጂ በህዝብ ዘንድ መንግስታዊ ተዓሚኒነት እንደሌለዉ ድርጅቱ ጠንቅቆ የተረዳዉ ነዉ።
ህዝብ ከመንግሰት የሚጠብቃቸዉ ባህሪያት አሉ። ከነዚህ የመንግሰት መመዘኛ ባሕሪያት የወረደ በስልጣን ላይ እስከቆየ የአገሩንና የህዝቡን ብሄራዊ ጥቅም ለባዕዳን አሳልፎ የሚቸረችር መንግስት እንደ ወራሪ/ቅኝ ገዢ ጦር፤ ወይንም እንደ ወሮበላ/ወንበዴ ከመታየት አያልፍም። መንግሰትና መሪዎች ለሚያስተዳድሩት ህዝብ ታማኝ እሰካልሆኑና ዘወትር በሸፍጥ፤በማጭበርበር፤ በመዋሸትና ሕዝብን በጠመንጃ አፈሙዝ አስፈራርቶ መኖርን ከ “ድል” በቆጠሩት ጊዜ አገርና ህዝብን የማስተዳደር የሞራል ብቃት እንዳጡ ያመላክታል።
ህወሃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ በፖለቲካ ተቃዋሚዎቹና ፖሊሲዎቹን በማይቀበሉ ወገኖች፤ በሲቪክ ማህበራትና በህዝብ ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የወሰዳቸዉን እርምጃዎች ጠቅለል አድርጎ የተመለከተ ሰዉ የመለስን መንግስት ከምን ሊፈርጀዉ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እስከመቼ በዚህ ዓይነት መቀጠል እንደሚፈልግና የስርኣቱ የመጨረሻ ግብ ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ከለት ወደለት የሚያነሱት ጉዳይ ሆኗል።
የጎሳ ፖለቲካ
ህወሃት/ኢህአዴግ ገና ከጅምሩ ለይስሙላ ባካሄደዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ጉባኤ ላይ ህብረ ብሄራዊ የዲሞክራሲ ሃይሎችን በማግለል፤ የጎሳ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማሰባሰብ የራሱን ጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ በህገ መንግሰትነት በመቅረፅ አገራዊ አንድነትን ለማጥፋት መነሳቱ ለጥቂቶች ከመመጀመሪያዉ ግልፅ ነበር፤ ለብዙ ሰዎች ዉሎ እያደር ነዉ የድርጅቱ አካሄድ የተገለፀላቸዉ።
ከኮሎኔል መንግስቱ ሀ/ማርያም 17 አመት የዘለቀ ትዉልድ የገደለ ወታደራዊ ጭቆና ተንፈስ የሚልበትን ቀዳዳ የናፈቀ ሕዝብ በምን ተዓምር በባሰ ደረጃ አገሩንና ወገኑን በቁም ገድሎ፤ በጣጥሶ፤ አፈር ምሶ የሚቀብር ስርኣት በምትኩ ስልጣን ለመጨበጥ በወገኖቹ አስከሬን ተረማምዶ ከበረሃ ይመጣል ብሎ እንደምን ሊያስብ ይችላል?
መለስና ድርጅታቸዉ ዛሬ እንደእንሰሳ በመቁጠር የሚረግጡት ሕዝብ ከደርግ አፈና የሚገላገልበትን ቀን በመናፈቅ፡ ወንበዴነታቸዉን አይቶ እንዳላየ ሲሆን፤ መዉጫ መግቢያ መንገድ ሲጠቁም፤ ቁራሽ ሲያቀብል፤”በቆርቆሮ ያለሽ?” ያገለገለ ልብስና ጫማዉን ሲሰጥ እንደኖረ ልቦናዉ ያዉቃል።
“ዛሬ የት ደረሱ? ምን ተፈጥሮ ይሆን?” በሚል የመረጃ ጥማቱ፤ መለስ ዜናዊና መንግስታቸዉ ዛሬ ከሩዋንዳዉ ሚል ኮሊንስ የሬዲዮ ጣቢያ ጋር አንድ አድርገዉ በመመልከት ” በዘር ማጥፋት ” ወንጀል የሚከሱትንና ስርጭቱን እንዲያቋርጥ ጥርሳቸዉን ነክሰዉ የሚታገሉትን የአሜሪካንና የጀርመን ድምፅ የአማርኛዉ አገልግሎቶች ምን ያህል ይከታተል እንደነበር በሚገባ ይታወቃል። ምን ይደረግ? ሕዝብ ያለመዉና ያገኘዉ በእጅጉ ተፃራሪ ሆነ፤ ‘ትሻልን ትቼ ትብስን’ ሆነበት እንጂ ።
በዚህ ምክንያት ታዲያ ዛሬ በቁም በመሞትና በመለመን ላይ ያለዉ የደርግ ሰራዊት ሽንፈቱ ሊያስከትል የሚችለዉ ዉጤት ይህ መሆኑን በወቅቱ ቢገነዘብ ኖሮ ህወሃት/ኢህአዴግን አመታት በፈጀ ሳይሆን ወራት በወሰደ ዉጊያ ማምከን ይችል እንደነበር በቁጭት የሚገልፁ አልታጡም።
ቋንቋን መሰረት ባደረገ የጎሳ አከላለል አገሪቱን ሸንሽኖ የህዝብን ታሪካዊ አንድነት ጥያቄ ዉስጥ በሚጥል የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል በሚል ሀረግ ለረዢም ጊዜ ተከባብረዉ በአንድነት በነበሩ ብሄረሰቦች መካከል በየምክንያቱ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
መንግስት በፌዴራል ክልሎች ዉስጥ ጣልቃ በመግባት የሚፈፅማቸዉ ማእከላዊ ቁጥጥሮች፤ የክልላዊ ድንበሮች መፈጠር፤ በግጦሽ መሬት፤ በዉሃ ፤ በደን ሀብትና በሌሎችም ጉዳዮች ያስከተሏቸዉ የይገባኛል ጥያቄዎች፤ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች በገፍ መፈልፈልና አገራዊ ጉዳዮች በሁለተኛ ደረጃ መታየታቸዉ፤ ያለ ጡረታና የአገልግሎት ካሳ በገፍና በግፍ የተሰናበቱ የደርግ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢህአዴግ መላ አገሪቱን በአንድ ጠባብ ብሄረሰብ የበላይነት ስር ለመቆጣጠር በየጊዜዉ የሚወስዳቸዉ ተግባራት ባለፉት 20 አመታት ዉስጥ ህዝባችንን ባላቋረጠ የሽብር ተግባር ዉስጥ እንዲኖር አስገድደዉታል።
በአማራና በኦሮሞ ብሄረሰቦች መካከል በአርባ ጉጉ በተቀሰቀሰዉ ግጭት፤ በሀረርጌ ሰላማዊ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይትና ከገደል እየተገፈተሩ እንዲገደሉ ሲደረግ
በሃረርጌ ወተር የኦሮሞ ተወላጆች ፤ በሰሜን ሃረርጌ በንግድ ይተዳደሩ የነበሩ የኢሳ ተወላጆች በግፍ መገደላቸዉ ይታወሳል። በኢሳና ጉርጉራ በተፈጠረዉ ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከደረሰዉ የሞትና የአካል ጉዳት ሌላ በኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ላይ የደረሰዉ አደጋ አይዘነጋም።
በኦጋዴን የሶማሌ ክልል ቀላፎ የሬር አባስ ነዋሪዎች ቤታቸዉ ተቃጥሎ፡ ከአካባቢዉ እንዲፈናቀሉ መደረጉ፡ እንዲሁም በጂጂጋ በጌሪና በጃርሶ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ መፈናቀሉ፡ በያቢሬ እና ኢሳቅ ነዋሪዎች መካከል ግጭቶች ተጭረዉ ሰዎች ከመኖሪያቸዉ መፈናቀላቸዉ፤ በቦረና ኦሮሞና በሶማሊዎች፡ በጉጂ፡ በጋምቤላ በአኝዋክና በኑዌር ጎሳዎች መካከል፤ እንዲሁም ከደገኛ ሰፋሪዎች ጋር ደም ያፋሰሱ የጎሳ ግጭቶች የመንግሰት ሽብርተኝነት ዉጤት ተደርገዉ የሚጠቀሱ ናቸዉ።
በአፋርና በድሬዳዋ አካባቢ በኦሮሞና በኢሳ ጎሳዎች መካከል በመሬት የይገባኛል ጥያቄ፤በአዋሳ የሲዳማ ብሄረሰብ አባላት ባነሱት የመብት ጥያቄ ምክንያት ዜጎች እርስ በርሳቸዉና ጣልቃ በገቡ የፀጥታ ሃይሎች ያለፍርድ ተገድለዋል።
የተወሰኑ የጎሳ የፖለቲካ ድርጅቶችን እራሱ በማደራጀትና አንዳንዶቹን የጥቅም ተጋሪዎቹ በማድረግ ኢህአዴግ በህዝቡ መካከል እንዲጫሩ ያደረጋቸዉ ግጭቶች በርካታ ናቸዉ። በቴፒ በሸኮ እና በመዠንገር ጎሳዎች መካከል በአረካና በአርባ ምንጭ በተፈጠሩ ግጭቶች ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያቸዉ ተፈናቅለዋል።
በጋምቤላ የመንግሰት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተሳተፉበት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በሁለት ቀናት ዉስጥ ቁጥራቸዉ 424 የአኝዋክ ብሄረሰብ አባላት ሲገደሉ ከ50 ሺህ የማያንሱ ወደ ሱዳን ፑቻላ የስደተኞች ካምፕ እንዲሸሹ ተደርገዋል። የግጭቱን መንስኤ ለተከታተለ ሰዉ የህወሃት/ኢህአዴግን መንግሰት ማንነት ለመረዳት አያዳግትም። መንገድ ባደፈጡ ዘራፊዎች የተገደሉ አንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደት ተመላሾች ጽ/ቤት ባልደረባና የአጃቢ ፖሊሳቸዉ አስከሬን ክልል ም/ቤቱ ድረስ እንዲመጣ ተደርጎ ለህዝብ እይታ እንዲቀርብ፤ ተመልካቹ ስሜቱ ከቁጥጥር ዉጭ እንዲሆንና ቁጣዉ እንዲቀሰቀስ ያደረገዉ መንግስት ለመሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ነዉ። ከዚህ አልፎ ጦር፤አካፋ፤ ገጀራ ቆንጨራና ያገኘዉን ስለት የያዘ ህዝብ በሆታ በመዉጣት በፀጥታ ሀይሎች ድጋፍና አጃቢነት፡ ያገኘዉን ሰላማዊ መንገደኛ ብቻ ሳይሆን የተዘጋ በር ሳይቀር እየሰበረ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከማስፈፀምና ሲፈፀም ከማየት ያለፈ ስለህወሃት/ኢህአዴግ መንግሰት ሽብርተኝነት ምን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል?
በአገሪቱ ላይ እንዳሻዉ ያለ ህዝብ ፈቃድ ማዘዝ
ሕወሃት/ኢህአዴግ ያለ ህዝብ ፈቃድና ተጠያቂነት እስከዛሬ የወሰዳቸዉንና የሚወስዳቸዉን ህገወጥ ተግባራት ለመዘርዘር አስቸጋሪ ነዉ። ላለፉት 20 አመታት ያለምንም ተጠያቂነት እራሱን ከህግ በላይ አድርጎ እንደሚቆጥር በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። በድርጅቱ፡ በጠ/ሚኒስትሩ ወይንም በፌዴራልና በክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ሳይሆን ጎዳና ላይ ህግ እንዲያስከብር የተሰማራ ተራ የፖሊስና የፀጥታ ሰራተኛ፤ አልፎ ተርፎ አንዳንድ ደካማ የገዢዉ መደብ ጎሳ ተወላጆች ሳይቀሩ እራሳቸዉን ከህግ በላይ አድርገዉ እንዲመለከቱ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ስርአት እንደሆነ ከህዝብ የተሰወረ አይደለም።
የራሱን የአንድ ክልል ጥቅም ለማስጠበቅ የአማራዉን ክልል በመቁረጥ ወደ ራሱ ከማካለሉም ሌላ አንድ የሆነዉን የአፋር ህዝብ በተለያየ ክልል ተከፋፍሎ እንዲኖር አድርጎታል።
ብሄራዊ ተዋፅኦ የነበረዉን የአገሪቱን ሰራዊት በማፍረስ በአብዛኛዉ በአንድ ጎሳ ጦር በመተካት በተለይም ቁልፍ የሆኑ ወታደራዊ የእዝ ስልጣኖችን በአንድ ብሄር ሙሉ ቁጥጥር ስር አዉሏል። ከዚህም በላይ ስመ ጥር የሆነዉን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተቋም ወደ ትግራይ በማዛወር፤ ታንኮችንና በርካታ ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎች ሳይቀር ማጓጓዙን ህዝብ ያዉቃል። ሃላፊነት ባልተሰማዉ መንገድ በሸጎሌና በደብረዘይት የመሳሪያ ዴፖዎች ላይ የደረሰዉን ዉድመት፤ በዚህም ከ800 ያላነሱ ሰዎች ህይወታቸዉን ማጣታቸዉ የተደበቀ ሚስጥር አይደለም። አገሪቱን በተቆጣጠረበት ማግስት ኢህአዴግ እንደመንግስት ሳይሆን እንደ አንድ የባዕድ ወራሪ ጦር ድርጅቶችን እየነቀለ፤ ንብረት እየዘረፈ ወደ ትግራይ ሲያሸሽ የታዘበዉ ህዘብ የደረሰበት ድምዳሜ “እዚህ ሆነ ወደ ትግራይ ወሰደዉ የአገር ሀብት የአገር ነዉ!” የሚል እንደነበር ይታወቃል።
በየገጠሩ ሙሉ በሙሉ ለአካባቢዉ የፖለቲካ ሃላፊዎች ተጠሪና ታዛዥ የሆነ የአካባቢ ሚሊሽያ በማደራጀት እስከ ገበሬ ማህበር የዘለቀ የፈላጭ ቆራጭነት ሃይሉን አስፋፍቷል። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በሚኖራቸዉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዉስጥ እንዲሁ ቁልፍ የሆኑ የስልጣን ቦታዎችን በራሱ በአንድ ጠባብ የጎሳ ቡድን አባላት አስይዟል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ሕዝብ ሳይወስንና “ምክር ቤት” ሳያዉቀዉ ድሃ ገበሬዎችን ለዘመናት ከኖሩበት ርስታቸዉ እንዲፈናቀሉ በማድረግ የኢትዮጵያን ድንበር ለሱዳን መንግስት አሳልፎ በመስጠት ያለህዝብ ፈቃድ በአገሪቱ ላይ እንዳሻዉ በአምባገነንነት ማዘዝ መጀመሩን ያሳያል።
“አዲሱ ቅኝ አገዛዝ ወይንም የመሬት ቅርምት” በሚል መጠሪያ በሚታወቀዉ ስልት በደቡቡ የሃገሪቱ ክፍል እጅግ ከፍተኛ ስፋት ያለው ድንግል መሬት ለውጪ ሃገር ከበርቴዎችና ኩባንያዎች ፍጹም ርካሽ በሆነ ዋጋ ለረዚም አመታት በኮንትራት እየተሰጠና እየተሸጠ፤ የአካባቢዉ የተፈጥሮ የደን ሃብት በመጨፍጨፍና በመቃጠል፡ የዱር አራዊቱ ከአካባቢዉ እንዲሸሹና በቦታው ላይ የነበሩት አነስተኛ ገበሬዎች እትብታቸዉ ከተቀበረበት ቀያቸው እየተገደዱ በመፈናቀል ላይ ይገኛሉ።
በተለይም ለአበባ ተክልና ለነዳጅ የሚሆኑ ዕፅዋትንና ሰብሎችን ለማምረት በጥቅም ላይ የሚዉለዉ መሬት የዉሃ እጥረትን፤የአፈር ንጥረ ነገር ዉድመትንና የአካባቢ አየር ብክለትን በማስከተል ለልጅ ልጆቻችን ሃላፊነት በጎደለዉ ተግባር ላይ የተሰማራ መሆኑ በየአጋጣሚዉ ቢገለፅም ክብደት ሰጥቶት በጉዳዩ ላይ ከባለሙያዎችና ከህዝብ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ አይደለም።
የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የኤርትራን መገንጠል ለማስፈፀምና ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ ለማድረግ ከጫካ የራሱን አጀንዳ ይዞ የመጣ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነዉ። በኤርትራ መገንጠል ላይ ያላቸዉን የተቃዉሞ ድምፅ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ኢህአዴግ በአደባባይ ተኩሶ ገድሏል፡ ዕድሜ ልካቸዉን ያፈሩትን ንብረት ተነጥቀዉ ከኤርትራ የተባረሩ ኢትዮጵያዊያን ጃን ሜዳ ሲሰቃዩ ለመብታቸዉ ያልቆመ መንግሰት፡ ኤርትራዉያን “ከባርነት ነፃነትን” ሊመርጡ የሚችሉበትን የድምፅ አሰጣጥ ለማመቻቸት መስቀል አደባባይ ድንኳን ጥሎ ደፋ ቀና ሲል እንደነበር አይዘነጋም።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የባድመ የድንበር ዉዝግብ ባስከተለዉ ግጭት ምክንያት በኢትዮጵያ ለረዢም አመታት የኖሩ ኤርትራዉያን ከስራ እንዲሰናበቱ፤ ጥቂቶች ቤተሰባቸዉንና ንብረታቸዉን እየጣሉ ከአገር እንዲባረሩ ከመደረጋቸዉም በላይ በርካታ ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል።
ከኤርትራ መገንጠል በፊት ሁለቱ ህዝቦች በአንድ ዜግነት ይኖሩ ስለነበር ህገ መንግስታዊ መብታቸዉንና አለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎችን በመፃረር የተወሰዱ እርምጃዎች እንደነበሩ ይታወቃል።
ከኤርትራ መገንጠል በሁዋላ በአሰብ ወደብና በአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ አጠቃቀም፤በኤርትራ በነበሩ የኢትዮጵያ የባንክ ቅርንጫፎች ሀብት፤ የህዝብ ተቀማጭና የብድር ሂሳብ ፤ በጡረታ ላይ የነበሩ ኤርትራዉያንን ጥቅም በማስጠበቅና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ህወሃት/ኢህአዴግ ያደረጋቸዉ ስምምነቶች ተጠያቂነትና ግልፅነት በሌለበት መልኩ የተፈፀሙ ነበሩ።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተቀሰቀሰዉ የድንበር ግጭት ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ኢህአዴግ የአልጄርሱን ስምምነት ከህዝብ ፍላጎት ዉጭ በመፈራረም የአገሪቱን ክፍል አሳልፎ መስጠቱ አይዘነጋም። በዚህ ጉዳይ 12 የሕወሃት አንጋፋ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ሳይቀሩ በወሰዱት አቋም በደም ከታገሉለት ድርጅት እንዲባረሩ መደረጉ ይታወሳል።
ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ጦርነት በዜጎች ህይወትና አካል ላይ ያደረሰዉ ኪሳራ ግምት ዉስጥ ሳይገባ በወታደራዊ ስንቅና ትጥቅ ብቻ 3.1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሰት ገልጿል። ይህ ሁሉ ኪሳራ የተከፈለበትን የሉአላዊነት መብት ግን ኢህአዴግ በአልጄርስ ባደረገዉ አግባብ ያልሆነ ስምምነት እንዲሁም ሄግ ለተሰየመዉ የአለም አቀፍ የድንበር ፍርድ ቤት ተቀባይነት የሌላቸዉን የቅኝ አገዛዝ ካርታዎች በማቅረብ አገራችን በጦርነት ያስመለሰችዉን ታሪካዊ መሬት በዉሳኔ እንድታጣ አድርጓታል። ሁለቱም አገሮች በጦርነቱ ከያዟቸዉ የጦር ምርኮኞች ዉስጥ በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል አማካይነት ባደረባቸዉ ህመም ምክንያት ከተለዋወጧቸዉ ዉጭ ዛሬም ያልተፈቱ እንዳሉ ይሰማል።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማፈራረስ
ተቃዋሚዎችን በተለያየ መንገድ በመዋጋትና ከሽግግር ወቅት ጀምሮ ሁሉንም በየደረጃዉ በመወንጀልና በማጥፋት ሰላማዊ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ሲፈፅም የነበረዉና በመፈፀም ላይ ያለዉ ድርጊት ህወሃት/ኢህአዴግ ህዝቡን እንደምን እንደሚመለከተዉና አገሪቱንም ምን ሊያደርጋት እንደሚፈልግ ለብዙዎች ግልፅ አይደለም ።
ዛሬ በአሸባሪነት ከሚወነጅለዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ጋር በሽግግር ወቅት አብረዉ እንደነበሩና ከጅምሩ ጤናማ ላልነበረ ግንኙነታቸዉ ይበልጥ መደፍረስ ተጠያቂዉ ማን እንደሆነ ህዝብ ጠንቅቆ ያዉቃል። በ1991/92 በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተከሰተዉን ችግር ለመፍታት በተደረሰዉ ስምምነት መሰረት ጦሩን በወታደራዊ ካምፕ ዉስጥ አላስገባም በማለት እራሱን የአገሪቱ ብሄራዊ የመከላከያ ሃይል ያደረገዉ የህወሀት/ኢህአዴግ ጦር በኦነግ ሰራዊት ላይ በቅድሚያ የጥቃት እርምጃ መዉሰዱንና ይህም ለቅራኔዎች መባባስና ለኦነግ ከሽግግር መንግስቱ መልቀቅ ምክንያት እንደሆነ ለማንም ሚስጥር አይደለም።
ህወሃት/ኢህአዴግ የራሱ ተለጣፊ ለሆነዉ የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ የፖለቲካ መደላድሎችን እየፈጠረ ከኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ዉጭ መለስና በዙሪያቸዉ ያሉት ትግራዮች በቀንደኛነት ኦነግንና በየደረጃዉ አገራዊ አንድነትን መሰረት አድርገዉ የተነሱ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግሬስን እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄ አባላትን ለብሄረሰባቸዉ መብትና ጥቅም በሰላማዊ መንገድ እንዳይታገሉ ሊያጠፏቸዉ ሌት ተቀን መማሰኑ የህዝቦች የነፃነት ትግል ጠላትነቱን በግልፅ ያሳያል።
ከኦነግ ጋር ቅርበት አለዉ የሚባለዉን የኦሮሞ ነፃነት እስላማዊ ግንባር የአመራር አባላትን በድሬዳዋ ከተማ መንገድ ዘግቶ እንደገደላቸዉ ይታወቃል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ከራሱ ወይንም እሱ በአምሳሉ ጠፍጥፎ ከሚያደራጃቸዉ በስተቀር ከየትኛዉም ብሄረሰብ ይሁኑ ወይንም ህብረብሄራዊ አደረጃጀት ይኑራቸዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች መንቀሳቀስ እንደሌለባቸዉ በመወሰን ባለፉት 20 አመታት ሲሰራ እንደነበር ግልፅ ነዉ። የህወሃት/ኢህአዴግ የጥቃት ኢላማ ያልሆነ ገለልተኛ የፖለቲካ ድርጅት እንደሌለ ኢትዮጵያዉያን በሚገባ ይረዳሉ።
ገና ከመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት/ኢዴህ/ በትግራይ ጽ/ቤት እንዳይከፍት መከልከሉን፡ የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት /መአህድ/ አባላቱን በእጩነት በየምርጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች እንዳያስመዘግብ መታገዱን፡የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር /ኦብነግ/ በሶማሌ ክልል በሚካሄደዉ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁነቱን በመግለፁ መንግስት የክልሉን ምርጫ ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉንና በድርጅቱና በአባላቱ ላይ የጥቃት ዘመቻ መክፈቱን አንዘነጋዉም።
በተቃዋሚነት በፈረጃቸዉ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ህዝብ በተቃዉሞ እንዲሰለፍና፤ ቅሬታ እንዲያቀርብ ይህንንም ምክንያት በማድረግ ድርጅቶቹን ለመዝጋትና ለማጉላላት፤ አባላቱን ለማስፈራራት እንዲሁም መሪዎቹን በሀሰት ክስ መስርቶ ለማሰርና ለፍርድ ለማቅረብ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደስልት መጠቀሙ አይጠፋንም። በፍርድ ቤትና ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በፀጥታ ሃይሎችና በያካባቢዉ በሚገኙ የአስተዳደር ጽ/ቤቶች አማካይነት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ጽ/ቤቶች እንዲዘጉና እንዲፈተሹ ወይንም እንዲዘረፉ ፤ መረጃዎች እንዲወሰዱ ይደረጋል።
በሶማሊ ክልል ይንቀሳቀሳሉ ያላቸዉን አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ እና የኦሮሚያ ነፃነት የእስልምና ግንባር የተባሉትን ለማጥፋት የኢትዮጵያ መንግስት በሙሉ ሃይሉ በመንቀሳቀስ ሶማሊያ የድንበር ከተማዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት እንደወጋቸዉ እናዉቃለን። እነዚህን ድርጅቶች ይደግፋሉ ያላቸዉን ሰላማዊ ዜጎች በተለይ በአዲስ አበባና በሶማሊ ክልል ዉስጥ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከማሰሩም በላይ በአዲሰ አበባና በአንዳንድ ስፍራዎች “ቦምብ አፈንድታችሁዋል” በማለት በሀሰት በአሸባሪነት ሲከሳቸዉ ቆይቷል።
ኦነግ፤የሲዳማ ነፃነት ንቅናቄ፤የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ቅንጅት/ኢድሃቅ/፤ ኦብነግ፤የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ፤ መላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት/መአህድ/ የኢትዮጵያ የሰላምና የዲሞክራሲ አማራጭ ሃይሎች ም/ቤት፤ በህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ያላሰለሰ ተቃዉሞና ወከባ ሲደርስባቸዉ እንደነበር እንዴት ሊዘነጋን ይችላል?
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ላለፉት ሃያ አመታት በትክክለኛዉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ስም የራሱን ደጋፊዎች በማደራጀት ህዝቡ በራሱ ብሄር/ብሄረሰብና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ አንድ አቋም እንዳይኖረዉ መከፋፈልን ሲፈጥር እንደነበር ይታወቃል።
በምርጫ ወቅት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፕሮግራማቸዉን ለህዝብ ማስተዋወቅ እንዳይችሉ በቂ ወይንም ተመጣጣኝ የአየር ጊዜ እንዳያገኙ ሲያደርግ፤ እራሱን ከህግ በላይ በማድረግ የአገሪቱን መንግስታዊ ተቋሞችና ንብረቶች እንዳሻዉ ሲጠቀም ነበር። ህወሃት/ኢህአዴግ በየአካባቢዉ በምክር ቤቶች ዉስጥ እና በሌሎች በመንግስት ታጣቂ ወይንም የፀጥታ ሃይል አባላት የሚጠበቁ ጽ/ቤቶች ሲኖሩት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ግን በግል ኪራይ ጽ/ቤት እንኳ እንዳያገኙ፤ከያዙም እንዲዘጉ ወይንም እንዲዘረፉ ሲያደርግ ቆይቷል።
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደርስባቸዉ ወከባ፤ እንግልትና የድምፅ መጭበርበር ምክንያት ሽንፈት እንዲገጥማቸዉ በማድረግ ህወሃት/ኢህአዴግ ግን በየጊዜዉ ከ80 በመቶ በላይ ድምፅ እንዳሸነፈ ተደርጎ እንዲቆጠር ራሱ ባደራጀዉ የምርጫ ቦርድ በሀሰት ሲያስወስን ለመኖሩ የሚካድ አይደለም።በዚህ ረገድ ሕዝብም ሆነ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችና እጩዎች በሚያሰሙት አቤቱታ እንዲ ታፈኑ፡እንዲታሰሩና እንዲገደሉም ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም።የአለም አቀፍ ታዛቢዎች በየትኛዉም የምርጫ ወቅት ነፃና ፍትሃዊ ነዉ ባላሉት የተጭበረበረ ምርጫ እራሱን በመንግሰትነት እንዳስቀመጠ እነሆ አራት የምርጫ ወቅቶችን አሳልፈናል።
ሙሉ በሙሉ በዚህ ተግባር የተወጠረ ድርጅት በመሆኑ ከዉጭ ከሚያገኘዉ መጠነ ሰፊ የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ አንፃር ባለፉት 20 አመታት አገሪቱን ከረሃብና ከድህነት ለመታደግ አንዳችም ፋይዳ ያለዉ ተግባር አልፈፀመም።
በሶማሊያ የተደረገዉ ጣልቃ ገብነት
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈዉን የሶማሊያ የፌዴራል የሽግግር መንግሰት ለመርዳት የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ የዉስጥ ጉዳይ እንደገባ ይታወቃል። በዚሁ ጣልቃ ገብነት በደቡብ ሶማሊያ ግዛት ዉስጥ በመስፋፋት ላይ ከነበረዉ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ንቅናቄ ጋር ግጭት በመፍጠር በዚህም ምክንያት ድርጅቱ በኢትዮጵያ ላይ የሃይማኖት ጦርነት እንዲያዉጅ ምክንያት ሆኗል። “ሽብርተኝነትን መዋጋት” በሚል ሽፋን የአሜሪካንን የዉክልና ጦርነት ለማካሄድ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲዘምት አድርጓል። ከልጅ ልጅ ሊሸጋገር የሚችል ቂምና በቀል ሊያሳድርና ጉርብትናችንን እስከመጨረሻዉ በሚያጠፋ ተግባር ወገኖቻችንን አላስፈላጊ ጦርነት ዉስጥ በመማገድ አስከሬናቸዉ እንደዉሻ በባዕድ ጎዳና ላይ እንዲጎተት የማይሽር የዜግነት ቁስል ጥሎብናል፤ የፓርላማ ተብዬዉ አባላት እንኳ በሶማሊያ ዉስጥ የሞቱት ወታደሮች ስንት እንደሆኑ ላቀረቡት ጥያቄ በጠ/ሚሩ የተሰጣቸዉ መልስ”ማወቅ አያስፈልጋችሁም” የሚል እንደነበር አይረሳንም።
በሌላ በኩል በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከባድ መሳሪያና በሮኬት በሶማሊያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እንዲተኩሱና እንዲገድሉ በመገደዳቸዉ ከ400 ሺህ ሰዎች በላይ ከአካባቢያቸዉ በመፈናቀል አብዛኛዎቹ እስላማዊ አማፅያኑን እንዲደባለቁ ምክንያት ሆኗል። በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰራዊት በበቀል በወሰደዉ እርምጃ ተቀጣጣይ ፈንጂ ሮኬት በከተማዉ ዉስጥ በመተኮስ አካባቢዎችንና ሰላማዊ ነዋሪዎችን ያለአንዳች መለየት ህፃናትና በእድሜ የገፉ አረጋዊያንን እንዳለ ሙሉ ቤተሰብን በአንድ ላይ እስከ ማጥፋት የፈፀመዉ ድርጊት ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር።
በአንድ የሞቃዲሾ መስጊድ ዉስጥ በመግባት በርካታ ሰዎችን ሲገድል የተወሰኑትን ሰዎች አንገታቸዉን እንደከብት በማረድ መግደሉን አለም አቀፍ መረጃዎች በወቅቱ እንዳስተጋቡት ይታወሳል።በሶማሊያ የያዛቸዉን የኤርትራ፤ የሶማሊያ፤ የኦጋዴን ሶማሌ ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እንደሚመረምርና አብዛኛዎቹ የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ ይነገራል።
በሶማሊ ክልል በመንግሰትና በኦብነግ ታጣቂዎች መካከል የነበረዉ ግጭት ተጠናክሮ በመቀጠሉ በነዳጅ ፍለጋ ስራ ላይ የተሰማሩ የቻይና ዜጎች፤ ለጥበቃ የተሰማሩ ወታደሮችና የአካባቢዉ ሰላማዊ ነዋሪዎች ተገድለዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጅጅጋና በደገ ሃቡር በተጠመዱ የቦምብ ፍንዳታዎች ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል። የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በወሰደዉ የበቀል እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በዘመቻ ገድሏል፡ ቤቶችን አቃጥሏል፡ የአርብቶ አደር ነዋሪዎችን የቤት እንሰሳት በሀይል ነድቶ ወስዷል፡ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል፡ የረድኤት ድርጅቶችን፤የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል አባላትና ገለልተኛ ጋዜጠኞች በአካባቢዉ እንይንቀሳቀሱ አግዷል፡፡
በህዝብ ተቀባይነት የሌላቸዉን ህጎች መደንገግ
ህወሃት/ኢህአዴግ የአገሪቱን ህዝብ አንድነት የሚጎዳዉን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትና እንዲሁም ገበሬዉን የመሬት ባለቤትነት የሚያሳጣዉን እርምጃ በህገ መንግስት ዉስጥ እንዲቀመጥ ማድረጉ በየጊዜዉ የሚጠየቅበትና “በእኛና በድርጅታችን መቃብር ላይ እስካልሆነ ድረስ በምንም ዓይነት የኢትዮጵያ ገበሬ መሬቱን ከመጠቀም ባሻገር የመሸጥና የመለወጥ መብት አይኖረዉም” በማለት በአገሪቱ 80 ከመቶ በሚሆነዉ አርሶ አደር መብት ላይ በብቸኝነት የፈረደ ድርጅት ነዉ።
የሲቪል ማህበራት፤ የፀረ ሽብርተኝነትና የፕሬስ ህጎች በመንግሰት ፖሊሲዎች ላይ ትችትና ተቃዉሞ እንዳይሰነዘር ለመከላከል፤ በዜጎች አስተሳሰብና እንቅስቃሴ ላይ ለዉጥ ማምጣት የሚችሉ ግለሰቦችን፤ ማህበሮችንና ጋዜጠኞችን ቀዳዳ ፈልጎ ለመወንጀል፤ ለማሰርና ለማንገላታት የፀደቁ ለመሆናቸዉ የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ የለም።
እኤአ በታህሳስ 2008 የወጣዉ የፕሬስ ህግ በምዝገባ፤ መረጃ በማግኘትና በሌሎችም ምክንያቶች ጋዜጠኞች ተግባራቸዉን በነፃነት እንዳያከናዉኑ ከማገዱም በላይ፤ ግልፅነት የጎደላቸዉን የወንጀል ድርጊቶች በመጥቀስ በጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የገንዘብ፤ የእስራትና የንብረት ዉርስ ቅጣቶችን ለመወሰን በሚያስችል መልክ የረቀቀና የፀደቀ መሆኑ ይታወቃል።
መንግስታዊ ያልሆኑ የዉጭ የእርዳታ ድርጅቶች በሰብኣዊ መብት፤ በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ መስራት እንዳይችሉ መንግሰት ባወጣዉ ህግ አግዷቸዋል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በብሄር ብረሰቦችና በዜጎች እንዲሁም በፆታና በሃይማኖት እኩልነት ላይ፡ በህፃናትና በአካል ጉዳተኞች መብት ላይ፤ በግጭት ማስወገድና በእርቅና ማስማማት ላይ፡ በህግና በፍትህ አፈፃፀም ላይ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ሆን በማለት ያወጣዉ ህግ አላማዉ ለማንም ግልፅ ነዉ። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በመጠቀም ሕወሃት/ኢህአዴግ እራሱ ወደ ስልጣን መምጣቱን ስለሚያዉቅ ለተቃዋሚ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ሽፋን ይሰጣሉ በሚል ግምት ያረቀቀና ያፀደቀዉ ህግ እንደሆነ ይታወቃል።
ከበጀታቸዉ 10% በላይ ከዉጭ የሚያገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደዉጭ ድርጅት ይቆጠራሉ” የሚለዉን ህግ የተቃወሙ አንድ ግለሰብ በቅርቡ በሰነዘሩት ትችት “ከበጀቱ ከ40-50% የሚያገኘዉ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግሰትስ የዉጭ መንግሰት መሆኑ ነዉ?” በማለት ያቀረቡት ጥያቄ አግባብ ነበር። አግባብ የሆነ መልሱም “አዎን!” ነዉ። ዜጎችን አፍኖና ረግጦ ለመግዛት ካለዉ እጅግ አረመኔያዊ ባህሪይ አኳያ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከዉጭ በሚያገኙት ርዳታ በሰብኣዊ መብት፡ በዲሞክራሲ፡ በመልካም አስተዳደር፡ በሴቶች፤ በሕፃናትና በወጣቶች ዙሪያ ትምህርትና ስልጠና እንዳይሰጡ፤ ነፃነት ገፋፊ የሆነ ህግና ደንብ የሚደነግግ ዘረኛ መንግስት የደቡብ አፍሪቃዉን አይነት የአፓርታይድ ዘረኛ የዉጭ መንግስት ከመሆን ሌላ ሊሆን አይችልም።
በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ላይ ፖሊስና የደህንነት ሃይሎች የጠረጠሩትን ሰዉም ሆነ ድርጅት ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዳሻቸዉ መፈተሽና የፈለጉትን ንብረት ነጥቀዉ የመዉሰድ መብት የሰጠ ስርኣት፤ አስፈላጊ ከሆነም በስልክ የሚጠየቅበት ነዉ። ስርዓተ አልበኝነትን በህግ ተፈፃሚ ማድረግ ከዚህ ዉጭ ምን ሊባል ይችላል?
ከስዬ እስር ጋር በተያያዘ የዋስ መብት እንዲነፈጋቸዉ በአስቸኳይ የፓርላማ ህግ፤ እንዲወጣ መደረጉ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚፈልጋቸዉን ሰዎች ለማጥቃት በፈለገዉ ጊዜ ለሚወስዳቸዉ ግብታዊ የፖለቲካ ዉሳኔዎች በቂ ምስክር ነዉ። የግንቦት 97 ምርጫ ዉጤትን ተከትሎ ቅንጅት ለፍትህና ለዲሞክራሲ የአዲስ አበባ ከተማን መስተዳድር ሙሉ በሙሉ ማሸነፉ እንደታወቀ፤ በታክስና የቀረጥ ገቢ፤ በንግድ፤ በመሬት አስተዳደር፤ በፖሊስና በሌሎችም በክፍለ ከተማዉ ስር የነበሩ ስልጣኖችን ወደ ፌዴራል መንግስት ለማዞር በምርጫ ህግ መሰረት ከምርጫዉ ቀደም ብሎ መፍረስ በሚገባዉ በማይመለከተዉ ተሰናባች ምክር ቤት አዲስ ህግ እንዲወጣ መደረጉ ምን ያህል የዘቀጠ ስራ እንደሚሰራ ይጠቁማል።
ነፃ ተቋማትን የፖለቲካ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ለማድረግ ማፈራረስ
አንጋፋ የሆነዉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ያላነሱ መምህራኑን በማባረርና አዲስ ቻርተር በማፅደቅ የነበረዉን የአካዳሚክ ነፃነት ለማዉደም ህወሃት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣ የወሰደዉ እርምጃ ለማንም ግልፅ ነዉ።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጉባኤን እንዲሁም በሰብአዊ መብት ላይ ትምህርት ለመስጠትና ለማስፋፋት የተቋቋመዉን አቡጊዳን ገና ከመጀመሪያዉ ሊያጠፋ መነሳቱ አይዘነጋንም። በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የተመሰረተዉ ኢሰመጉ የፖለቲካ ወገንተኛና የአማራ ድርጅት(ለነገሩ ቢሆንስ?) እንደሆነ በሌላም በኩል የተቃዋሚዎች ደጋፊ እንደሆነ መንግስት በሚያካሄደዉ የስም ማጥፋት ዘመቻ የምዝገባ ፈቃድ ነፍጎት እንደነበር አይረሳንም። የኦሮሞ ሰብኣዊ መብት ካዉንስል እና ገዳዶ በሚል መጠሪያ የተቋቋሙ ድርጅቶችንም እንዲሁ የስራ ፈቃድ እንደነፈጋቸዉ ይታወቃል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ያልፈለጋቸዉን 45 የአገር ዉስጥና 2 የዉጭ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፈቃዳቸዉ እንዳይታደስና ስራቸዉን እንዲያቆሙ አድርጓል። ከዚሁ ጋር የኦሮሞ የረድኤት ድርጅት በኦሮሚያ ክልል ም/ቤት ትእዛዝ ጽ/ቤቶቹን በሙሉ እንዲዘጋ ተደርጓል።
በተቃራኒዉ የህወሃት የእርዳታ ድርጅት ኤፈርት በሚል መጠሪያ የኢንቬስትሜንት ፤የንግድና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ሚቆጣጠርበት ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ አነስተኛ ነጋዴዎች ከንግዱ አለም እንዲሰናበቱ በማድረግ ላይ ይገኛል። ሙሉ በሙሉ የመንግሰት ድጋፍ እንዲያገኙ፡ መሬትና የድርጅት ጽ/ቤት ያለ ኪራይ፡ የባንክ ብድር ያለ ምንም ዋስትና ፡ ከታክስና ግብር ነፃ እንዲሆኑ፡ የመንግስት የፋይናንስ የጨረታ ደንብና ሕግ ሳይጠበቅ በቀጥታ ያለ ዉድድር የጨረታ አሸናፊ እንዲሆኑ፡ የጉምሩክ ቀረጥ እንዳይመለከታቸዉ በማድረግ በኤፈርት ስር የተዋቀሩት ከ35 በላይ የሆኑት የህወሃት የንግድ ተቋሞች የአገሪቱን ፖለቲካ ለመቆጣጠር ኢኮኖሚዉን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር በሚለዉ ፍልስፍና መሰረት አገሪቱን በግል ንብረትነት ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት መደራጀታቸዉ አይካድም። ብዙ የንግድ የሽርክና ድርጅቶች ህዝብ እያወቀ በግለሰቦች ስም የንግድ ፈቃድ ወጥቶላቸዉ በመስራት ላይ እንዳሉ ግልፅ ነዉ።
አክሽን ፕሮፌሽናል ፎር ዘ ፒፕል፤ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትና የሰላም ማእከል፡ የኢትዮጵያ ምክር ቤት/ኮንግሬስ/ ለዲሞክራሲ እና ኢንተር አፍሪቃን ግሩፕ የተባሉት የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ትምህርት፤ ስልጠና እና ክትትል የሚያደርጉ ድርጅቶች የህወሃት/ኢህአዴግን መንግስት በየጊዜዉ ስለሚተቹት ብቻ ትልቅ የስም ማጥፋትና ማስፈራራት ሲደርስባቸዉ እንደነበር ከማናችንም የተሰወረ አይደለም።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርና የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን በትምህርትና በኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች ሽፋን የመንግሰት የጥቃት ኢላማ ሆነዋል። የድርጅቶቹን ጽ/ቤቶች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በመዝጋት፤ አመራሮቹን በማሰር እንዲሁም የባንክ ሂሳባቸዉን እንዳያንቀሳቅሱ በማድረግ አልፎ ተርፎም በስማቸዉ ሌሎች ተመሳሳይ ተለጣፊ ድርጅቶችን በራሱ አባላትና ደጋፊዎች እንዲመሰረት በማድረግ እንዳፈረሳቸዉ ይታወቃል። ብዙዎቹ አካባቢያቸዉን እየለቀቁ እንዲሄዱና ቤተሰባቸዉን ጥለዉ ከአገር እንዲኮበልሉ ተገደዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት የነበሩትን ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያትን “በጦር መሳሪያ አመፅ ለመፍጠር”በሚል የሃሰት ክስ እስር ቤት እንደወረወራቸዉ ይታወሳል።አለም አቀፍ የሰራተኞች ማህበር በሁለቱ ማህበራት ላይ ህወሃት/ኢህአዴግ የወሰደዉ እርምጃ አገሪቱ የፈረመቻቸዉን አለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚፃረር ተግባር መሆኑን በመግለፅ ተቃዉሞዉን አሰምቷል።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በአገሪቱ ያለዉ የፍትህ ስርኣት በተለይም አስገድዶ መድፈርንና ሌሎች የሴቶችን መብት በተመለከተ መሻሻል እንዳለባቸዉ ጥያቄ በማቅረቡና በሌላ በኩል አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነች ወጣትን “አፈቀርኩ” በማለት በወጣቷና በቤተሰቧ ላይ ከፍተኛ (በሁዋላም እስከሞት የደረሰ) ችግር በፈጠረ አንድ የገዢዉ ጎሳ አባል ቤተሰብ ልጅ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ጠንከር ያለ እርምጃ ባለ መዉሰዱ ያለዉን ቅሬታ ያሰማል። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ማህበሩ ከተፈቀደለት ቻርተር ዉጭ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በመግለፅ የፍትህ ሚኒስቴር ለተወሰነ ጊዜ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን በማገድ፡ በባንክ የሚገኝ ገንዘቡን እንዳያንቀሳቅስ መወሰኑ አይረሳም።
የሰብኣዊ መብት ሊግ፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች የትብብር ኮሚቴ፡ የኦሮሞ የቀድሞ እስረኞች የሰብኣዊ መብት ማህበር፤ የኦጋዴን የሰብአዊ መብት ኮሚቴ በመንግስት ወከባ ሲፈፀምባቸዉ እንደነበርና እንዲዘጉ መደረጉ ይታወሳል።
የኦሮሞ እራስን በራስ የመርጃ ድርጅት የሜጫና ቱሌማ ማህበር ፈቃዱ ታግዶ አመራሩ በሽብርተኝነት እስር ቤት እንደገባ አይዘነጋም። ሌሎቹን የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች በተለያየ መንገድ በማሰወገድ መንግሰት የራሱን የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽንና የኡምቡድስማን ጽ/ቤት በማቋቋም የምክር ቤት አባላት ተቃዉሞ እያቀረቡ የራሱ ደጋፊ የሆኑት ዶ/ር ካሳ ገ/ህይወት እና አባይ ተክለ በየነ የተባሉ ሰዎች እንዲመሯቸዉ አድርጓል።
ክልሎች የመንግስትን ፖሊሲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማይቀበሉ ወገኖች ላይ በግምገማና በሃሰት ክስ በመመስረት ያለህግ ማሰር፤ ከስራ ማሰናበትና አንዳንድ የሲቪል መብቶችን እንዲገፉ መብት እንደሰጣቸዉ ይታወቃል።
ህወሃት/ኢህአዴግ የሚያደራጃቸዉ ተለጣፊ ድርጅቶች ቀድሞ የነበሩ ድርጅት አመራሮችን ጽ/ቤቶች፤ ንብረትና የባንክ ሂሳብ እንዲያስረክቧቸዉ በመጠየቅ ተቃዉሞ ሲገጥማቸዉና ግጭት ሲከሰት መንግሰት ጣልቃ በመግባት ህጋዊ የሆኑትን በማባረርና በማሰር ሃላፊነትና ንብረቱን በኢህአዴግ በስዉር ለተቋቋሙት አሳልፎ ይሰጣል።
በመሰብሰብና ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ መብት ላይ የሚፈፀመዉ አፈና
ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎችን የማካሄድ በህገ መንግስቱ ላይ እራሱ በአዋጅ ያስቀመጠዉን መብት እያንዳንዱ ክልል በዘፈቀደ እንዲከለክል አድርጓል።
የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይሰበሰቡ፡ አባላቶቻቸዉን ሰብስበዉ ገለፃ እንዳያደርጉ ይከለከላሉ።አንዳንዴም በስብሰባ ላይ ሆነዉ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ይከበባሉ፡ መንግስት በሚያሰማራቸዉ ሃይሎች አማካይነት በቁጥጥር ስር ይዉላሉ።
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአካዳሚክ ነፃነት ዉስጥ መንግስት ያለዉን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ጥያቄ በማቅረባቸዉ፤ በቅጥር ግቢዉ ዉስጥ የሰፈሩት የመንግስት ወታደሮች እንዲለቁ እንዲሁም ከመንግስት ጋር የቀረበ ግንኙነት የነበራቸዉ የተማሪዎች አስተዳደር ሰራተኞች እንዲሰናበቱ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ መንግስት በወሰደዉ እርምጃ ሌሎች ሲቪሎችን ጨምሮ ከ40 በላይ ተማሪዎች ተገድለዋል።
ኢህአዴግ በአገሪቱ የሚገኙትን የመገናኛ ብዙሃን በሞኖፖል ይዞ የራሱ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ መሳሪያዎች ከማድረግ ዉጭ የአገሪቱ ህዝብ ሀሳቡን በነፃነት የሚገልፅበት ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል። ቁጥራቸዉ ብዙ የሆነ ነፃ ጋዜጠኞች፤ አሳታሚዎችና ድሀ ጋዜጣ ሻጮች ሳይቀሩ በፖሊስ፤ በፀጥታና በደህንነት ሃይሎች እየታደኑ እስራት፤ ግርፋትና ድብደባ ደርሶባቸዋል። ሕይወታቸዉን አሳልፈዉ የሰጡ፤ አንጡራ ቅርሳቸዉን ሽጠዉና ለዉጠዉ በሀሰት ክስ የተበየነባቸዉን የገንዘብ ቅጣት የከፈሉና ከመኖሪያ ቤታቸዉና ከጽ/ቤታቸዉ ኮምፒዩተር፤ ካሜራና ሌሎችንም ንብረቶች እንደተወረሱ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ።
በግንቦት 97 የተካሄደዉን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ህወሃት/ኢህአዴግ በቁጥጥር ስር ባዋላቸዉ የነፃዉ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ የመሰረተዉ ክስ፤ “ህገመንግስቱን በመፃረር፤ የአገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ በመጣል፤ በህዝቦች መካከል የርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር በማነሳሳት፡ የአገር ክህደትና የዘር ማጥፋት ” የሚሉ እንደነበርና እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ እስራት የተፈረደባቸዉ እንደነበሩ ከህዝብ የተሰወረ አልነበረም።
የምርጫዉን ዘገባ አዛብታችሁዋል በሚል ክስ ለአሜሪካን ድምፅና ለዶቼ ቬሌ የአማርኛዉ አገልግሎች የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች በወቅቱ የስራ ፈቃዳቸዉን መነጠቃቸዉ ይታወሳል።
ከምርጫ 97 በሁዋላ በነፃ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰዉ እስር ወከባና የሃሰት ክስ ከሚገባዉ በላይ ገደቡን እያለፈ በመሄዱ አንዳንዶች እራሳቸዉን ከሙያዉ ሲያገልሉ፤ጥቂቶች እንዳይሰሩ በመንግሰት ፈቃድ ሲከለከሉ፤ አባላቱ በጠቅላላዉ ማለት ይቻላል ከቀጣይ ክስና አፈና ለመዳን አገር ለቀዉ ወደ ዉጭ እንዲኮበልሉ ተገደዋል።
አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት አስጠባቂ ድርጅት /ሲፒጄ/ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለማችን አገራቸውን ጥለው ወደ ዉጭ አገሮች በተሰደዱ ጋዜጠኛች ቁጥር ኢትዮጵያ ቀዳሚዉን ስፍራ መያዟን አስታዉቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በዉጭ ጋዜጠኞች ላይ የሚከተለዉ እርምጃ በተመሳሳይ ሁኔታ አይን ያወጣ ነበር። የዉጭ የዜና ወኪሎች በየአመቱ የስራ ፈቃዳቸዉን እንዲያድሱ መመሪያ ከማዉጣት አልፎ፤ በኢትዮጵያ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የዉጭ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር ሆነዉ የተመረጡት የቢቢሲ ጋዜጠኛ አሊስ ማርቲን በተመረጡ በ3ኛዉ ቀን የስራ ፈቃድ ተከልክለዉ እንዲባረሩ ማድረጉ አይዘነጋም። ብዙ የዉጭ ጋዜጠኞች ህወሃት/ኢህአዴግን የሚነቅፉና የሚተቹ ዘገባዎችን በማቅረባቸዉ ከአገር እንደተባረሩ እናዉቃለን።
ከዚህ በተጨማሪ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬድዮ የአማርኛዉ አገልግሎቶችን፤ የግንቦት ሰባትንና የሌሎች ተቃዋሚ ድርጅት የሬድዮ ጣቢያዎችን እንዲሁም ብቸኛና ገለልተኛ የሆነዉን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዢንን በመደጋገም በማፈን ላይ እንዳለ ይታወቃል።
የኢንተርኔት የመረጃ መረቦች እንዲሁ በኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነት የሚጠቀምባቸዉ እንዳይሆኑ ተደርገዋል።
በዜጎች ላይ የሚፈፀመዉ ሰቆቃ፤ እስራት፤ ግርፋትና ግድያ
በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች በየክልሉ በተቋቋሙ እስር ቤቶች ዉስጥ ክስ ሳይመሰረትባቸዉ እንደሚታሰሩና፤ ግርፋት ሰቆቃና ድብደባ እንደሚደርስባቸዉ አልፎ ተርፎም እንደሚገደሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ አይደለም።
በደብረ ዘይት የኢትዮጵያ አየር ሃይል የበረራ ትምህርት ሲሰጡ ዉለዉ ወደ ቤታቸዉ ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ በወያኔ/ኢህአዴግ የስራ ባልደረቦቻቸዉ ታፍነዉ ተወስደዉ ለሁለት አመት ያህል በጭለማ ቤት ዉስጥ ብቻቸዉን ታስረዉ የደረሰባቸዉን እዉነተኛ ታሪክ ከተለቀቁ በሁዋላ ከአገር ሸሽተዉ ዛሬ በስደት ከሚገኙበት ለህዝብ ካሳወቁት ከሌ/ኮሎኔል ተሾመ ተንኮሉ የበለጠ ለዚህ በዜጎች ላይ ለሚፈፀመዉ ግፍ በህይወት ያለ ምሰክር ሊጠራ የሚችል አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ የህግ አስፈፃሚዉ አካላት የሆኑት ፖሊሰ፤ ጦሩ፡ ፍርድ ቤቶችና ወህኒ ቤቶች በህወሃት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ሙሉ በሙሉ ከመዉደቃቸዉ ሌላ የአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት እንኳ ሊያዛቸዉ እንደማይችል በተለያየ ወቅት ተመስክሯል።
የፖሊስ ጣቢያዎች፤የአስተዳደር ጽ/ቤቶች፤ወታደራዊ ካምፖች፡ ህጋዊ እስር ቤቶች፡ ሚስጢራዊ ስዉር እስር ቤቶች፡ በሀገረ ማርያም፤ ሁርሶ፤ ዴዴሳ፤ አጋርፋ፤ ዝዋይ፤ ጦላይ፤ቃሊቲ፤ማእከላዊ፤ በየክልል ወህኒ ቤቶችና በተለይ በአዲስ አበባ ዘመናዊ ቪላዎች በመከራየት በእስር ቤትነት ከመጠቀሙም በላይ በእስረኞች ላይ ሰቆቃ፤ ግርፋትና ድብደባ መፈፀሚያ በማድረግ እንደሚገለገልባቸዉ ይታወቃል። የኢህኣፓ አባላትን በትግራይ ዉስጥ ባደራጀዉ ድብቅ እስር ቤት ዉስጥ እንዳስቀመጣቸዉና እስከዛሬ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ በመደጋገም ተገልጿል። አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ድርጅት እንዳይጎበኛቸዉ መንግስት ፈቃድ እንደከለከለም ይታወቃል። ህወሀት/ኢህአዴግ የራሱን አባላት ሳይቀር በነዚሁ ምስጢራዊ እስር ቤቶች ዉስጥ እንደሚያሰቃያቸዉ ዉስጥ አዋቂዎች ይመሰክራሉ።
ለሰላም ኮንፈረንስ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የኢድሃቅ አባል አበራ የማነአብ ያለፍርድ ቤት ዉሳኔ እኤአ ከታህሳስ 1993 ጀምሮ በእስር እንዲሰቃዩ ተደርጓል። ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ጨምሮ በርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እስር ቤት ተወርዉረዋል።ከፕሮፌሰር አስራት ሌላ አራት ሰዎች በመንግስት ላይ በጦር መሳሪያ የተደገፈ ጦርነት ለማካሄድ ተንቀሳቅሳችሁዋል በማለት መከሰሳቸዉ ይታወቃል። ፕሮፌሰር አስራት በእስር ላይ በ70 አመት እድሜያቸዉ በስኳርና በልብ ህመም እየተሰቃዩ ባሉበት ወቅት በአገር ዉስጥ የሚገኙና በዉጭ የሂዩማን ራይትስ ዎች ተሟጋቾች እንዲፈቱ ጥያቄ እያቀረቡ ባለበት “የጦር መሳሪያ አመፅ ለማስነሳት” በሚል ህወሃት/ኢህአዴግ ሌላ 2ኛ ክስ በመመስረት በእስር ቤት እንዲቆዩ አድርጓል።ይሁን እንጂ በሽታቸዉ ስር ከሰደደ በሁዋላ ወደ ዉጭ አገር ሄደዉ እንዲታከሙ ቢፈቅድም ከስድስት ወራት በሁዋላ በፊላደልፊያ ሆስፒታል ዉስጥ ህይወታቸዉ አልፏል።
የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አባተ ኪሾ እንዲሁ ከነስዬ ዘመዶችና የክልል ጉዳይ ሃላፊ ከነበሩት ቢተዉ በላይ ጋር በተያያዘ እስር በቤት በሙስና ወንጀል ተከሰዉ መታሰራቸዉ ይታወቃል።
የአለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ድንጋጌም ሆነ ህወሀት/ኢህአዴግ ያፀደቀዉ የአገሪቱ ህገ መንግሰት በማንም ሰዉ ላይ ሰቆቃ፡ ግርፋትና ድብደባ እንዲሁም ጭካኔ የተመላበት ኢሰብኣዊ ድርጊትም ሆነ ስብዕናን የሚያዋርድ ተግባር ሊፈፅምበት እንደማይገባ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ ይህ በእስራት ወቅትና ከእስራት ዉጭ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች፤ የደህንነት፤ የፖሊስ፤ የድርጅቱ ካድሬዎችና ወታደሮች አማካይነት በመላዉ የአገሪቱ ክልሎች በዜጎች ላይ የሚፈፀም የየቀኑ ተግባር ነዉ። ይህን በመፈፀም ማእከላዊ የምርመራ ድርጅት በመባል የሚታወቀዉ እስር ቤትና የደህንነት ተቋም የናዚ ጀርመን ይጠቀምባቸዉ ከነበሩት የማጎሪያ ካምፖች ያልተናነሰ እንደሆነ ይነገራል።
እኤአ በ2009 ” መፈንቅለ መንግሰት ለማካሄድ ሲያሴሩ ደረስኩባቸዉ ” ባላቸዉ የግንቦት 7 የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አባል እንደሆኑ በገለፃቸዉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪሎች ላይ የተቃዋሚዬ ወላጅ አባታ ቦሆኑት የ80 አመት አዛዉንት ላይ እንዲሁም ” የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ ኦነግ/ አባል ወይንም ደጋፊዎች ናችሁ” ተብለዉ በቁጥጥር ስር በዋሉ ግለሰቦች ላይ የተፈፀሙት ተግባሮች ሰብኣዊነት የጎደላቸዉ እንደነበሩ በዉስጥ አዋቂ የምርመራ ክፍል ተቆርቋሪዎች መገለፁ ይታወሳል።
በኤሌክትሪክ ገመድና በሌሎችም ነገሮች በመጠቀም እጆቻቸዉ የፊጢኝ በሰንሰለትና በካቴና ታስረዉ፡ግድግዳ ላይ በተመቱ ምስማርና ችካሎች እንዳይንቀሳቀሱ ተወጥረዉ፤ የዉስጥ እግራቸዉንና መላ አካላቸዉን በጠቅላላ አዕምሯቸዉን እስኪስቱ ድረስ ተደብድበዋል።
በኤሌክትሪክ ሰዉነታቸዉ እንዲነዝር፤ ወንዶች በብልቶቻቸዉ ላይ ክብደት ያላቸዉን እቃዎች እንዲያንጠለጥሉ እንዲሁም በብርድ ለሰዓታት አይኖቻቸዉን ታስረዉ ዉጭ እንዲቆሙ ተደርገዋል። በዘዴ የኤች አይ ቪ ኤይድስ ቫይረስ ተጠቂ ሊደረጉ እንደሚችሉ እንዲሁም መሳሪያ በላያቸዉ ላይ በመተኮስ የመግደል ማስፈራራት እንደደረሰባቸዉ ተገልጿል። ሴት እስረኞች ጠርሙስ የመሳሰሉትን መጠቀምን ጨምሮ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ተገደዉ ተደፍረዋል።
እስረኞች የጤና ምርመራና የህግ ምክር ማግኘት ብዙዉን ጊዜ አይፈቀድላቸዉም። በተለይ አንዳንድ እስረኞች ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዉ ብቻቸዉን በተዘጋ ክፍል ዉስጥ ለጤና ተስማሚ ባልሆነ መንገድ እንዲሰቃዩ ይደረጋል።
ሌሎች ሰዎችን በወንጀለኛነት እንዲጠቁሙ የሚገደዱበት ወቅት እንዳለ ይታወቃል። እስረኞች እነዚህና ሌሎችም ኢሰብኣዊ ሰቆቃ፡ድብደባ፤ ግርፋትና ማስፈራራት ሲበዛባቸዉ ያልፈፀሙትን ወንጀል ፈፅመናል በማለጥ ተገደዉ እንዲፈርሙ ይደረጋል፡ ይህም በፍ/ቤቶች ተቀባይነት እንዲያገኝ እየተደረገ ንፁህ ዜጎች ሞት፤ የእድሜ ልክ ወይንም የረዢም አመታት እስራት ይፈረድባቸዋል።
በእስር ቤት በግርፋትና ድብደባ ከሞቱት መካከል የመአህድ አባል ገብረሀና ወልደመድህን እንዲሁም ሄኖክ ዮናታን በታሰረበት ነጆ ወህኒ ቤት መገደሉ፤ ሁለት ልጆቹ ተይዘዉ ተደብድበዉ የተገደሉበት ጃፈር ኢብራሂም በምስራቅ ኦሮሚያ በመንግስት ወታደሮች ከተያዘ በሁዋላ በማግስቱ አስከሬኑ ተጥሎ መገኘቱ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸዉ።
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ሱዳን፤ ኬንያ፤ ሶማሊያ፡ ጅቡቲ ድረስ ድንበር ዘልቀዉ በመግባት የሚፈልጓቸዉን ስደተኞች አፍነዉ መዉሰዳቸዉና ሊያመጧቸዉ ያልተሳካላቸዉን እንደሚገድሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ያዉቀዋል።
የመንግስት የፀጥታ አስከባሪዎች፤ ታጣቂዎች፤ ወታደሮች በቀን በአደባባይ የመንግስትን የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አጥብቀዉ የሚቃወሙ ናቸዉ በሚሏቸዉ ላይ ግድያ እስከመፈፀም ያልተገደበ መብት አላቸዉ። አሊ ዩሱፍ የተባሉ የኦነግ አባል አዲስ አበባ ሱቃቸዉ ደጃፍ ላይ ተገድለዋል።
በአምቦ ከተማ የተገደሉት ደራራ ከፈኒ፤የመምህራን ማህበሩ አሰፋ ማሩ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ። በትግራይ ባለፈዉ ምርጫ ወቅት በመኖሪያ ቤቱ የተገደለዉ የአረና ትግራይ አባል የተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ አረጋዊ ገብረዮሃንስ ከሚጠቀሱት መካከል ነዉ።
ከጂቡቲ መንግስት ጋር ባደረገዉ ስምምነት የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናትን በማምጣት ለፍርድ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በሌላ በኩል ሰላማዊ ህዝብን በቦምብ እንዲደበድቡ የተሰጣቸዉን መመሪያ ባለመቀበል ጅቡቲ ገብተዉ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪዎችን ህወሃት/ኢህአዴግ ከጂቡቲ መንግስት ተረክቦ ወዴት እንዳደረሳቸው እስከዛሬ አይታወቅም፡፡
ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ህወሃት/ኢህአዴግ ምርጫዉን በማጭበርበር በሃይል ስልጣን ከመያዙ ባሻገር ድምፃችን ይከበር በማለት አደባባይ የወጡ ከ193 በላይ ንፁህ ዜጎችን መግደሉን ከ700 በላይ በሚሆኑት ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱንና በሺዎች የሚቆጠሩትን ለእስር መዳረጉ፤ ጨዋ የተከበሩ አዛዉንቶችን ሳይቀር በአንድ ምላጭ ፀጉራቸዉን እንደላጫቸዉ እራሱ ባቋቋመዉ አጣሪ ቡድን በማስረጃ መጋለጡ አይዘነጋም።
የግንቦት 97 ብሄራዊ ምርጫን ተከትሎ የምርጫዉ አሸናፊ የሆነዉን የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የቅንጅት የአመራር አካላትን፤ ጋዜጠኞችን፤ የምርጫ ታዛቢዎችንና የሰብአዊ መብት ድርጅት አባላትን በ”አመፅ መንግስት ለመገልበጥ አሲራችሁዋል” በማለት በ”አገር መክዳትና በዘር ማጥፋት” ወንጀል ሰብስቦ በሀሰት ክስ እሰከ እድሜ ልክ እስራት በይኖባቸዉ እንደነበር አይዘነጋም። ክስ ከተመሰረተባቸዉ መካከል 35 ሰዎች በዉጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ከነዚህ ዉስጥ አምስቱ የአሜሪካን ድምፅ የአማርኛዉ አገልግሎት ጋዜጠኞች እንደነበሩ ይታወቃል።
በ2010 የተደረገዉን የተጭበረበረ ምርጫ ተከትሎ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግሬስን፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄንና የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ/ መኢአድ/ አባላትን በየገበሬ ማህበሩ የማህበራዊ ችሎቶችን በማቋቋምና ክስ በመመስረት በአካባቢዉ በሚገኙት የህወሀት/ኢህአዴግ አባላት የቅጣት ዉሳኔ እንደሚፈርድባቸዉ እናዉቃለን። በምርጫዉ ኢህአዴግን ያልደገፉ ድሃ ገበሬዎች ማዳበሪያና ሌሎች የእርሻ ግብኣት ድጋፎች እንዳይደረጉላቸዉ መከልከላቸዉን የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች አጋልጠዋል።
በእያንዳንዱ የገበሬ ማህበር ቤት እየዞሩ ኢህአዴግን መምረጥ እንዳለባቸዉ በማስጠንቀቅ፡ ያለበለዚያ ምንም አይነት የመንግሰት አቅርቦት እንደማያገኙ፤ ቤተሰቡ የመስራትም ሆነ የመማር እድል እንደማይኖረዉ በግልፅ ያስጠነቅቁ እንደነበር ይታወቃል።
ከምርጫዉ በፊት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መስራች የሆኑት ወ/ት ብርቱኳን ሚዴቅሳ የተሰጣቸዉ ምህረት እንዲነሳ ተደርጎ በእድሜ ልክ እስራት ወህኒ ቤት እንዲወረወሩ መደረጉና ኢህአዴግ ምርጫዉን 99.6% መቆጣጠሩን ካረጋገጠ በሁዋላ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዉስጥ ምንም ተሳትፎ እንዳያደርጉ ሰብኣዊ መብታቸዉን ጨፍልቆ ግልፅ ባልሆነ የግዳጅ ፊርማ እንደለቀቃቸዉ ይታወሳል።
ማጠቃለያ
ኢህአዴግ የፖለቲካ አላማዉን ለማስፈፀም ላለፉት 20 አመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ በደህንነትና በወታደራዊ ተቋሞቹ አማካይነት የአገሪቱን ፖለቲካ በግሉ ለመቆጣጠር፡ በጎሳና በዘር ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም በማካሄድ፡ በፖለቲካና በሲቪክ ማህበራት ድርጅቶችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈፅማቸዉ የነበሩትና ዛሬም የሚፈፅማቸዉ የሽብር ተግባሮች ለመሆናቸዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያዉቃል።
አገሪቱን በየደረጃዉ ስርኣተ አልባ አድርጎ ሸርሽሮ ለዉድቀትና ለዉድመት ከማመቻቸቱ ባሻገር የማትላቀቀዉ አገራዊ ነቀርሳ ወደ መሆን ደረጃ በመሸጋገር ላይ እንዳለ ለመተንበይ ነቢይነትን አይጠይቅም።
እናም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሰት “በሽብርተኝነት” “የአገርን ሰላም በማደፍረስ” “ህገ መንግስታዊዉን ስርአት በመናድ ” “በዘር ማጥፋት” “በአገር መክዳት” ወዘተ… የሚሉትን የወንጀል ክሶች የሚጠቀምበት ለምን አላማ እንደሆነ ግልፅ በመሆኑ ማንንም ሊያስበረግግ አይችልም። አሸባሪዉ ማን እንደሆን ህዝብ ጠንቅቆ ያዉቃል። ገደቡን አልፎ በመፍሰስ ላይ ያለዉ ግፍና በደል ከቁርት የቁጣ ቀኑ ጋር እስኪያገጣጥመዉ የታፈነ ዜጋ ሁሉን እያወቀ እንዳላወቀ መሆን ግዴታዉ ነዉና።
አመሰግናለሁ።

አስተያየታችሁን በሚከተለዉ አድራሻ ግለፁልኝ። negussiegamma@yahoo.com
No comments: