Theme images by kelvinjay. Powered by Blogger.

Slider

ESAT

Ethiopian News

Movies

Drama

Sport

Opinion

History

» » » » » » የጀግናው ኮ/ል አብዲሳ አጋ አስገራሚ የህይወት ታሪክ

ኮ/ል አብዲሳ አጋ

ጀግናው ኮ/ል አብዲሳ አጋ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ዛሬ አርባ አንድ አመት ሞላዉ። ይሄን ታሪክ ከአፄ ቴወድሮስና ከበላይ ዘለቀ ታሪክ እኩል ስሰማዉ ያደኩት እዉነተኛ የጀግንነት ታሪክ ነዉ።

አብዲሳ አጋ በ1928 ዓ/ም የጣልያን ወረራ ወቅት ተማርኮ ወደ ጣልያን ከተወሰደ በኋላ ብርድ ልብሱን ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት አምልጦ በርካታ ጀግንነቶችን የፈጸመ የኢትዮጵያ ወታደር ነው። ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው በ1912 ዓ.ም ፣ ወለጋ ነበር።

በ12 ዓመቱ አባቱ በንዴት ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አብዲሳ አባቱን ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ በሞት ተቀጥተዋል። በኋላም በ14 ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገሉን ሀ ብሎ ጀመረ።  


አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ ከሁለት አመት በኋላ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን ለመከላከል በ16 ዓመቱ ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ።

ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር።  

በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ተደረገ።

አልሸነፍ ባይነት መለያው የሆነው አብዲሳ ሁሊዮ ከተባለ ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት እስር ቤት ለማምለጥ ማሰላሰል ጀመረ። ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ አገር እንደሚጠብቀው ቢያውቅም በነጻነቱ የማይደራደረው አብዲሳ የተሰጠውን የብርድ-ልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል አመለጠ።

ከዛ በኋላ ግን ሽሽት አልነበረም የጀመረው አብዲሳ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በማታ ወደ እስር ቤቱ በመመለስ ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞቹን በመሉ ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር።  

ያመለጡት እስረኞች ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች በወሰዱት መሳሪያ በመታገዝ የአማጽያን ጦር ያደራጁ ሲሆን ጦሩን እንዲመራም የመረጡት ጀግናውን አብዲሳን ነበር። ከዛም የተለያዩ የጣልያን ወታደራዊ ሠፈራዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ወራሪዎቹ ጣልያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የአርበኛ እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው ያጋጥማቸው ጀመር።

በአብዲሳ ጦር እጅግ የተረበሹት ጣልያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት ውጊያውን እንዲያቆም እና የነሱን ጦር እንዲቀላቀል ለምነውት ነበር። አብዲሳ ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን እንደማይቆም በማስረገጥ ጥያቄውን ውድቅ አደርጎ ጣልያኖችን በሀገራቸው ማስጨነቅ ቀጠለ።

በወቅቱ እየተጋጋለ የመጣው የጀርመን ናዚ ሥርዓት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲጀምር ፋሺስት ሙሶሎኒ ከጀርመኖች ጋር ሲያብር እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገሮች የሕብረት ጦር መስርተው የሙሶሎኒን ጦር መውጋት ጀምረው ነበር።

በወቅቱ ይህ የሕብረት ጦር የአብዲሳን ዝና በመስማታቸው ጣልያንን ለማዳከም ለአብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፎች ማድረግ ጀመሩ። 

በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎለት ነበር።

ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። 

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግሥታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። አብዲሳ ግን ኢትዮጲያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ህዝቡን እና መንግስቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ውድቅ አደረገ።  

በዚህ የተናደዱ ምዕራብውያንም በፈጠራ ወንጀል ከሰው ወደ እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ከተከፈለ በኋላ በክብር ወደ ሃገሩ ሊመለስ ችሏል። 

ወደ ኢትዮጲያ ከተመለሰ በኋላ ሰራዊቱን በቅንነት ያገለገለው አብዲሳ በኮኔልነት ማዕረግ የአጼ ሃይለስላሴ ልዩ ጠባቂ ጦር እየመራ ቆይቶ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ ከጥቂት አመታት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

ጽሁፉ ከፌስቡክ የተገኘ ነው

«
Next
Newer Post
»
Previous
Older Post

No comments:

Leave a Reply